የኢትዮጵያና የአውሮፓ ቢዝነስ ፎረም በመጪው ሳምንት በቤልጂዬም ብራሰልስ ይካሄዳል ተባለ

84

አዲስ አበባ ግንቦት 2/2011 በኢትዮጵያና አውሮፓ መካከል ያለውን የንግድና ኢንቨስትመንት ግንኙነት ለማጠናከር የሚያስችል የቢዝነስ ፎረም በመጪው ሳምንት በቤልጂየም ብራሰልስ እንደሚካሄድ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታወቀ።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ አቶ ገዱ አንዳርጋቸው በተቋሙ ሚኒስትር ሆነው ከተሾሙ ወዲህ የመጀመሪያ የውጭ ጉብኝታቸውን በሱዳን ካርቱም ማድረጋቸውም ተገልጿል። 

የሚኒስቴሩ ቃል አቀባይ ፅህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ነቢያት ጌታቸው በወቅታዊ የአገሪቱ ውጭ ግንኙነት ጉዳዮች ዙሪያ ዛሬ መግለጫ ሰጥተዋል።

ቃል አቀባዩ በዚሁ መግለጫቸው ከመጪው ሳምንት ማክሰኞ ግንቦት 6 ቀን ጀምሮ ለሁለት ቀናት በብራሰልስ በሚካሄደው የኢትዮጵና አውሮፓ ቢዝነስ ፎረም ላይ ኢትዮጵያ ያላትን የኢንቨስትመንት አማራጮች በተመለከተ ከአውሮፓ ባለሃብቶች ጋር ምክክር ይደረጋል።

በመድረኩ ላይ የኢትዮጵያና አውሮፓ አገራት የንግድና ኢንቨስትመንት ማህበረሰብ አባላትም እንደሚሳተፉ ቃል አቀባዩ ገልፀዋል።

ኢትዮጵያ ከአውሮፓ አገራት ጋር ስትራቴጂያዊ የሆነ የትብብር ግንኙነት እንዳላትም አውስተዋል።

አክለውም የአሜሪካ መንግስት በኢትዮጵያ የተጀመረውን ለውጥ በተለይም የኢኮኖሚ ዘርፉን  መደገፍ የሚችልባቸውን መንገዶች ማሳየትን ያለመ መድረክም በመጪው ሳምንት ግንቦት 7 እና 8 ቀን 2011 ዓ.ም በዋሽንግተን ዲሲ ይካሄዳል ብለዋል።   

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ገዱ አንዳርጋቸው በተቋሙ ሚኒስትር ሆነው ከተሾሙ ወዲህ የመጀመሪያ የውጭ ጉብኝታቸውን በተያዘው ሳምንት በሱዳን ማድረጋቸውንም  ተናግረዋል።

ሚኒስትሩ በሁለት ቀናት የካርቱም ጉብኝታቸው ከሱዳን ወታደራዊ የሽግግር ምክር ቤት ሊቀመንበር ሌተናል ጄኔራል አብዱል ፈታህ አል ቡርሃን፣ ከሱዳን ''የነጻነት እና የለውጥ ሃይሎች'' ተወካዮች እንዲሁም በሱዳን ሰላማዊ የስልጣን ሽግግር እንዲመሰረት ከሚሰሩ ታዋቂ አካላት ጋር የተናጥል ውይይት አድርገዋል።

በዚህም ኢትዮጵያ በሱዳን የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ ሳትገባ የሱዳንን ሉዓላዊነት በማክበር  የሱዳንን ህዝብ ፍላጎት መሰረት አድርጋ አስፈላጊውን ድጋፍ ለማድረግ ቁርጠኛ መሆኗን ገልጸዋል።

ሚኒስትሩ በሱዳን በነበራቸው ቆይታ የኢትዮጵያ ማህበረሰብ ማቆያና ማገገሚያ ማዕከል በመጎብኘት በማዕከሉ ከሚገኙ ኢትዮጵያዊያን ጋር ውይይት አድርገዋል።

ቃል አቀባዩ አክለውም 67ኛው የምስራቅአፍሪካ የልማትበይነ መንግስታት (ኢጋድ) ሚኒስትሮች ምክር ቤት ስብሰባ ሚያዝያ 29 ቀን 2011 ዓ.ም በጁባ መካሄዱን ጠቅሰው በዚህም የአገሪቱ ፖለቲካ ተደራዳሪ ወገኖች ባለፈው ወር በአዲስ አበባ ባደረጉት ውይይት ቀሪ ስራዎችን በቀጣዩ ስድስት ወራት ጊዜ ውስጥ ለማጠናቀቅ የጊዜ ገደብና አመላካች ነጥቦችን በግልጽ በማስቀመጥ ለመፈጸም ስምምነት ላይ መድረሳቸውን ገልጸዋል።

የሳኡዲ አረቢያ መንግስት የረመዳን ጾምን ምክንያት በማድረግ የረጂም ጊዜ ፍርድ ተፈርዶባቸው የነበሩ 1400 ኢትዮጵያውያን የህግ ታራሚዎች በምህረት መለቀቃቸውንም ቃል አቀባዩ አንስተዋል።

በተጨማሪም አሁን በእስር ላይ የሚገኙ ቀሪ ታራሚዎች የእስር ጊዜያቸው በ75 በመቶ  እንደሚቀንስላቸው የአገሪቱ ባለስልጣናት ማሳወቃቸውን አቶ ነቢያት ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም