የኢህአዴግ ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ የኢኮኖሚ ማሻሻያ እርምጃዎችን ለመውሰድ የሚያስችሉ አቅጣጫዎች አስቀመጠ

104
አዲስ አበባ ግንቦት 28/2010 የኢህአዴግ ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አሁን ከተደረሰበት የዕድገት ደረጃ ጋር የሚመጣጠን የኢኮኖሚ ማሻሻያ እርምጃዎችን ለመውሰድ የሚያስችሉ አቅጣጫዎችን አስቀመጠ። ከማሻሻያዎቹ መካከል የአገር ውስጥ ባለሃብቶች በሜጋ ፕሮጀክቶች ላይ የአክስዮን ድርሻ እንዲኖራቸው የሚያስችለው ውሳኔ ተጠቃሽ ነው። የኢህአዴግ ምክር ቤት ጽህፈት ቤት የስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ዛሬ ያካሄደውን መደበኛ ስብስባ በማስመልከት ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት በላከው መግለጫ እንዳስታወቀው፤ ኮሚቴው በኢትዮጵያ የኤኮኖሚ ማሻሻያ እርምጃዎችን ለመውሰድ የሚያስችሉ ቀጣይ የአፈጻጸም አቅጣጫዎችን አስቀምጧል። ኢትዮጵያ ላለፉት 15 ዓመታት ፈጣንና ተከታታይ ዕድገት ማስመዝገብ መቻሏን የገለጸው ኮሚቴው፤ ይህም ዕድገት ከፍተኛ መነቃቃትንና ተነሳሽነትን በመቀስቀስ የአገር ውስጥ እና የውጭ ኢንቨስትመንት እንዲጠናከር ዕድል መፍጠሩን አውስቷል። በአንፃሩም ደግሞ በቀጣይ ከፍተኛ ትኩረት የሚሹ ጉዳዮች ያሉ መሆኑን ኮሚቴው በጥልቀት ገምግሟል። የውጭ ምንዛሬ ግኝትን ማስፋት፣ የገቢ መሰብሰብ አቅምን ማሳደግ፣ የኑሮ ውድነት ችግርን ማቃለልና የመልካም አስተዳደር ችግሮችን መፍታት ትኩረት የሚሹ ጉዳዮች ስለመሆናቸው ኮሚቴው በስፋት ተወያይቷል። በዚህም መሰረት የእስካሁኑን ፈጣን ዕድገት ይበልጥ ለማስፋት እና ለማጠናከር እንዲሁም በተሻለ የወጪ ንግድ አፈጻጸም ለመድገም "አሁን ከተደረሰበት የዕድገት ደረጃ ጋር የሚመጣጠን የኢኮኖሚ ማሻሻያ እርምጃዎችን መውሰድ እንደሚያስፈልግ ይታመናል" ሲል መግለጹን መግለጫው አትቷል። ባለፉት ሁለት ዓመት ተኩል የወጭ ንግድ አፈጻጸም ከታቀደው በታች መሆኑን ያወሳው መግለጫው፤ በዚህ ረገድ ያለውን ውስንነት ለመፍታትም የግብርናና ኢንዱስትሪ አምራች ዘርፍን ምርትና ምርታማነት ማሳደግ አስፈላጊ መሆኑን አጽንኦት ሰጥቶታል። በተለይም የወጭ ምርቶች ላይ መረባረብ እንደሚጠይቅ ገልጿል። በዚህም መሰረት ፈጣን ዕድገቱ ዜጎችን አካታች በሆነ መልኩ ግለቱን ጠብቆ እንዲቀጥል የአገር ውስጥ ባለሃብቶች በሜጋ ፕሮጀክቶች ላይ የአክስዮን ድርሻ እንዲኖራቸው አቅጣጫ መቀመጡን አስታውቋል። በመንግስት ይዞታ ሥር ያሉና በማምረት ወይም አገልግሎት በመስጠት ላይ የሚገኙትም ሆነ በግንባታ ላይ የሚገኙ የባቡር፣ የስኳር ልማት፣ የኢንዱስትሪ ፓርክ፣ የሆቴል እና የተለያዩ የማኑፋክቸሪንግ ድርጅቶች ሙሉ በሙሉ ወይም በከፊል በአክሲዮን ሽያጭ ወደ ግል ዘርፍ እንደሚተላለፉም ጠቁሟል። እንዲሁም የኢትዮ-ቴሌኮም፣ የኢትዮጵያ አየር መንገድ፣ የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫዎች እና የባህር ትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ድርጅት ትልቁን የአክስዮን ድርሻ መንግስት ይዞ ቀሪው አክሲዮን ለአገር ውስጥ እና ለውጭ ባለሃብቶች እንዲተላለፉ እንደሚደረግም በመግለጫው ተጠቅሷል። የኢህአዴግ ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ያስቀመጠው አቅጣጫ በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን እና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ለረጅም ጊዜያት በአገራቸው ልማት ለመሰማራት ያላቸውን ምኞት እንደሚያረጋግጥ አብራርቷል። የኢኮኖሚውን ዕድገት ፍጥነት ይበልጥ ለማስቀጠል፣ እንዲሁም እውቀትና የውጭ ምንዛሪ ካፒታል ያላቸው የውጭ ባለሃብቶች ተገቢውን አዎንታዊ ሚና እንዲጫወቱ ለማድረግ እንደሚያስችልም አስታውቋል። በመግለጫው እንደተገለጸው፤ አፈፃፀሙም የልማታዊ መንግስት ባህሪያትን በሚያስጠብቅ መልኩና የኢትዮጵያን ፈጣንና ተከታታይ ዕድገት እንዲሁም ዘላቂ ጥቅም በሚያረጋግጥ ሁኔታ እንዲመራ ታስቦ የሚሰራ ነው። ለዚህም ዝርዝሩ በባለሙያዎች ተደግፎ በጥብቅ ዲሲፒሊን ተግባራዊ እንዲደረግ የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴው አቅጣጫ ማስቀመጡን ጽህፈት ቤቱ የላከው መግለጫ አመልከቷል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም