ተደራጅተው በሚንቀሳቀሱ ሰዎች የሚፈጸም ስርቆት መበራከት በኑሮአችን ላይ ስጋት ፈጥሮብናል -የደብረታቦር ከተማ ነዋሪዎች

71

ባህር ዳር  ግንቦት 1 / 2011 ተደራጅተው በሚንቀሳቀሱ ሰዎች የሚጸፈም ስርቆት መበራከት በእለት ከእለት ኑሮአቸው ላይ ስጋት እንደፈጠረባቸው አንዳንድ የደብረታቦር ከተማ ነዋሪዎች ገለጹ።

 የከተማው አስተዳደር 'ስጋቱ ከአራት ወራት በፊት የነበረውን ሁኔታ እንጂ፤የአሁኑን ተጨባጭ ሁኔታ አያመለክትም''ብሏል።

አንዳንድ የከተማው ነዋሪዎች በወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ ዛሬ ከአስተዳደሩ ጋር ሲወያዩ እንዳስረዱት በከተማዋ ተደራጅተው በሚንቀሳቀሱ ሰዎች የሚፈጸም ስርቆት በእለት ከእለት ኑሮአቸውቸው ላይ ጫና ፈጥሯል።

ከነዋሪዎች መካከልም ወጣት ታፈረ ዋለ በከተማው ከምሽቱ አንድ ሰዓት በኋላ ለመንቀሳቀስ የማይቻልበት ሁኔታ መፈጠሩን ተናግሯል፡፡

"በምሽት መንቀሳቀስ በራስ ህይወትና ንብረት እንደመፍረድ ይቆጠራል" ያለው ወጣቱ፣ ተደራጅተው የእጅ ስልክ(ሞባይል)የሚነጥቁና ሌሎች ንብረቶችን አካላዊ ጉዳት በማድረስ የሚዘርፉ ሰዎች መበራከታቸውን ገልጿል።

የጸጥታ መዋቅሩም ሆነ አመራሩ የማስተካከያ እርምጃ ለመውሰድ ቁርጠኝነት እንደማይታይባቸውም አመልክቷል፡፡

ሌላው የከተማው ነዋሪ አቶ ካሳሁን አያሌው ከተማዋ ከሁለት ዓመት በፊት ሰላሟ የተረጋገጠና የኮንፈረንስ ከተማ እንደነበረች አስታውሰዋል።

አሁን ላይ የተደራጁ ቡድኖች በሚፈጥሩት ዝርፊያ ጸጥታ ስጋት ላይ መውደቁንና ነዋሪውም በነፃነት የሚንቀሳቀስበት ሁኔታ መገደቡን አስረድተዋል።

ዘራፊዎች ተይዘው ለህግ ሲቀርቡም ተገቢና አስተማሪ እርምጃ እንደማይወስድባቸው በመግለጽ።

በከተማዋ የሚስተዋለውን ስርቆት ለመከላከል የጸጥታ መዋቅሩና ነዋሪዎች በጋራ መስራት እንደሚገባቸውም አሳስበዋል።

አቶ ደሳለኝ አልታሰብ የተባሉ የከተማው ነዋሪ በበኩላቸው የአስተዳደሩ በዝርፊያ ወንጀል የተሰማሩ ሰዎችን ተከታትሎ በመያዝ በኩል ችግር ይታይበታል ይላሉ። 

"የእኔ ብቻ የሚለው አስተሳሰብ ዳብሯል" ያሉት እኚሁ አስተያየት ሰጪ፣መስረቅ ጸያፍና በወንጀል እንደሚያስጠይቅ ያለመረዳት ችግር እንደሚታይ ገልጸዋል።

የከተማው ምክትል ከንቲባ አቶ አበበ እምቢአለ በበኩላቸው ነዋሪዎች የሚያነሱት ችግር ከአራት ወራት በፊት የነበረውን የከታማው ሁኔታ እንጂ፤የአሁኑን ተጨባጭ ሁኔታ አያሳይም ብለዋል።

ቀደም ሲል በባጃጅ በመንቀሳቀስ በደብደባ ጭምር የሚዘርፉ የተደራጁ ሰዎች እንደነበሩ ያስታወሱት ምክትል ከንቲባው፣ ችግሩን በጥናት በመለየትና አጥፊዎችን ለህግ በማቅረብ  ችግሩን በተወሰነ ደረጃ መፍታታቸውን ገልጸዋል፡፡

የከተማውን ነዋሪዎች፣ወጣቶችና የጸጥታ አካላትን በጋራ በማቀናጀት በከተማዋ ሰላምና ጸጥታ ሥራ  በማሳተፋቸው ችግሩ መቀነሱን አስረድተዋል።

በአሁኑ ሰዓት አልፎ አልፎ ዝርፊያ እንደሚፈጸም ያመኑት ምክትል ከንቲባው፣ ችግሩን ሙሉ በሙሉ ለማስቆም የጸጥታ መዋቅሩ እየተጠናከረ መሆኑን ተናግረዋል።

"ቀደም ሲል የተፈጠረው ስጋት አሁንም በኅብረተሰቡ ዘንድ አልጠፋም " ያሉት አቶ አበበ፣ችግሩን በቅርበት በመገምገምና በማስተካከል ከተማዋ ሰላሟ የተረጋገጠ ለማድረግ ጥረቱ እንደሚቀጥልም አስታውቀል።


ደብረ ታቦር ከ600ዓመታት በላይ ዕድሜ ያስቆጠረች፣በአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥትየደቡብ ጎንደር ዞን ዋና ከተማ ናት።

ከተማዋ ከ200ሺህ በላይ ነዋሪዎች እንዳሏት መረጃዎች ያመለክታሉ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም