9 መቶ ሺህ የሚጠጉ ተፈናቃዮች ወደ ቀያቸው ተመልሰዋል - መንግስት

126

አዲስ አበባ ግንቦት 1/2011 በተለያዩ የኢትዮጵያ ክፍሎች በተከሰቱ ግጭቶች ሳቢያ ከቤት ንብረታቸው የተፈናቀሉ 9 መቶ ሺህ የሚጠጉ ዜጎች ወደ ቀያቸው እንዲመለሱ ማድረጉን መንግስት አስታወቀ።

ግጭቶችን በመፍጠርና ዜጎችን በማፈናቀል ሂደት ላይ እጃቸው አለበት የተባሉ ከ2 ሺህ በላይ ተጠርጣሪዎች መለየታቻውን የጠቅላይ ሚኒስትር ፅህፈት ቤት አስታውቋል።

ከእነዚህ ውስጥ 1 ሺህ  300ዎቹ ህግ ጥላ ስር አንደሚገኙ የጽህፈት ቤቱ የፕሬስ ሴክሪታረያት ኃላፊ አቶ ንጉሱ ጥላሁን ዛሬ በሰጡት መግለጫ ተናግረዋል።

ባለፉት ሁለት ዓመታት ጊዜ ውስጥ በተለያዩ የአገሪቱ ክፍል በሚሊዮን የሚቆጠሩ ዜጎች ተፈናቅለዋል።

ተፈናቃዮች በተጠለሉበት ቦታ ለከፋ ችግር እንዳይጋለጡ መንግስት አስፈላጊውን ድጋፍ ማድረጉንም አቶ ንጉሱ ተናግረዋል።

መንግስት ጊዜ ወስዶ ዜጎችን ለመመለስ የሚያስችሉ ምቹ ሁኔታዎችን ለመፍጠር ሲሰራ መቆየቱን የጠቆሙት አቶ ንጉሱ፤ አስካሁን ባለው ሂደት 9 መቶ ሺህ የሚጠጉ ተፈናቃዮችን ወደ ቀያቸው መመለስ ተችሏል ብለዋል።

ተፈናቃዮችን የመመለሱ ስራ እራሳቸው ተፈናቃዮችን ባሳተፈ መልኩ እየተከናወነ መሆኑንም አክለዋል።

ተፈናቃዮቹን የመመለሱ ስራ እንከን እንዳይገጥመው መንግስት የራሱን ድርሻ እንደሚወጣ አብራርተው፤ አንድም ዜጋ ያለፈቃዱ ወደቀየው እንዲመለስ አይደረግም ብለዋል።

ተፈናቃዮቹ ወደቀያቸው ተመልሰው እስኪቋቋሙ ድረስም የመንግስት ድጋፍ እንደሚቀጥል አውስተዋል።

መጪው ጊዜ ክረምት ከመሆኑ ጋር ተያይዞ የሚከሰቱ በሽታዎችን ለመከላከል የ5 ነጥብ 2 ቢሊዮን ብር መድሃኒት ግዢ እየተከናወነ መሆኑንም የፕሬስ ሰክረታሪየቱ ኃላፊ ለአብነት አንስተዋል።

መንግስት በዚህ ትጋት ላይ እያለ አዳዲስ ግጭቶች እንዲፈጠሩና ተፈናቃዮች ወደ ቀያቸው እንዳይመለሱ የሚንቀሳቀሱ አካለት በተጨባጭ መኖራቸውን ጠቁመው፤ እነዚህ አካላት ላይ አስፈላጊው እርምጃ እንደሚወሰድም አስጠንቅቀዋል።

በዚህ ህገ-ወጥ  ተግባር ላይ የሚሳተፉ አካላት አብዛኛዎቹ በማፈናቀሉ ሂደት ላይ እጃቸው ያለበት  አካላት መሆናቸውን በመጠቆም።

ዜጎችን ወደ ቀያቸው ከመመለስ ጎን ለጎን በማፈናቀሉ ሂደት ላይ እጃቸው አለበት ተብለው የሚታሰቡ 2 ሺህ 517 ተጠርጣሪዎችን ተለይተዋል ያሉት አቶ ንጉሱ፤ ከእነዚህም ውስጥ 1 ሺህ 300 የሚሆኑት በህግ ጥላ ስር እንደሚገኙ ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ በሽግግር ላይ እንደመሆኗ የሚታዩ ችግሮች ሁሉ በአንድ ጀምበር ማስተካከል እንደማይቻልም አውስተዋል።

"ነገር ግን መንግስት የህግ የበላይነትን ለድርድር አያቀርብም፤ ይህን ቀይ መስመር የሚያልፉትንም ተጠያቂ ያደርጋል" ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም