ሸገርን የማስዋብ የእራት ገበታ የፊታችን ግንቦት 11 ይካሄዳል- ጠቅላይ ሚኒስቴር ጽህፈት ቤት

90

አዲስ አበባ ግንቦት 1/2011 የተለያዩ አለም አቀፍ ድርጅቶች፣ ኤምባሲዎችና የልማት ተቋማት አዲስ አበባን ለማስዋብ ለተጀመረው መርሃ ግብር ድጋፍ እያደረጉ መሆኑን የጠቅላይ ሚኒስትር ፅህፈት ቤት አስታውቋል።

የጠቅላይ ሚኒስቴር ጽህፈት ቤት ፕሬስ ሴክሬተሪ ሃላፊ አቶ ንጉሱ ጥላሁን ዛሬ በሰጡት መግለጫ እንደተናገሩት፤ መንግስት የኢትዮጵያን ከተሞች ለዜጎች ምቹና ጽዱ መኖሪያ እንዲሆኑ ለማድረግ እየሰራ ይገኛል።

በተለይም አዲስ አበባን በማስዋብ ስራ ንጹህ አየር ለመተንፈስ የሚረዳ፣ ንጹህ ውሃ በከተሞች እንዲፈስ የሚያደርግ፣ የቱሪዝም መስህብ የሚሆንና በሂደትም የስራ እድል ለመፍጠር የሚያስችል ፕሮጀክት ለማከናወን መንግስት እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

ለፕሮጀክቱም የተለያዩ አለም አቀፍ ድርጅቶች፣ ኤምባሲዎችና የልማት ተቋማት ድጋፍ በማድረግ አጋርነታቸውን እያሳዩ መሆናቸውንም ነው የገለጹት።

የተባበሩት መንግስታት የልማት ፕሮግራም (ዩኤንዲፒ) እና የተባበሩት መንግስታት የኢንዱስትሪ ድርጅት (ይኒዶ) 1 ሚሊዮን ዶላር፣ የአፍሪካ ልማት ባንክ 600 ሺ ዶላር እንዲሁም የጣልያን መንግስት ደግሞ 5 ሚሊዮን ዩሮ ድጋፍ አድርገዋል።

የቻይና መንግስትም በበኩሉ ለፕሮጀክቱ የዲዛይንና የ12 ኪሎ ሜትር ለመሸፈን ቃል መግባቱንም ጠቁመዋል።  

ለፕሮጀክቱ  በአገር ውስጥ ያሉ 200 የተለያዩ ተቋማትና ግለሰቦችም በገንዘብና በጉልበት አስተዋጽኦ ለማበርከት ጥረት እያደረጉ መሆኑን ተናግረዋል።

ከዚሁ ፕሮጀክት ጋር በተያያዘም በአገር ውስጥ የሚገኙ ተቋማትና ግለሰቦች ድጋፋቸውን ለማረጋገጥ የሚሳተፉበትና "የሸገር ገበታ" በሚል የተዘጋጀ የእራት መርሃ-ግብር የፊታችን ግንቦት 11 ቀን 2011 ዓ.ም በብሄራዊ ቤተመንግስት የሚካሄድ መሆኑን ይፋ አድርገዋል አቶ ንጉሱ።

በአዲስ አበባ ሰባት ታላላቅ ወንዞችን ጨምሮ 76 የሚሆኑ ወንዞች የሚገኙ ሲሆን ወንዞቹ ከመኖሪያ ቤቶችና ከተለያዩ ተቋማት በሚወጡ ደረቅና ፈሳሽ ቆሻሻዎች ለከፍተኛ ብክለት የተዳረጉ ናቸው።

ይህንን ችግር ለመፍታት ታስቦ ለተቀረፀውና በሶስት ዓመታት ጊዜ ውስጥ ይጠናቀቃል ተብሎ ለሚጠበቀው ሸገርን የማስዋብ ፕሮጀክት 29 ቢሊየን ብር ወጪ ይጠይቃል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም