የሐይቅ ከተማ ነዋሪዎች መኖሪያ ቤት ለመገንባት መስፈርት ብናሟላም ቦታ እላገኘንም አሉ

53


ደሴ ግንቦት 1/ 2011 ''የመኖሪያ ቤት መስሪያ ቦታ ለማግኘት የሚያስፈልገንን መስፈርት ብናሟላም ምላሽ ባለማግኘታችን ለችግር ተዳርገናል'' ሲሉ በደቡብ ወሎ ዞን የሐይቅ ከተማ ነዋሪዎች ተናገሩ።

የነዋሪዎችን የቦታ ጥያቄ  ለመመለስ ጥረት እየተደረገ መሆኑን የዞኑ ቤቶች ልማትና ኮንስትራክሽን መምሪያ አስታውቋል፡፡

በሐይቅ  ከተማ የቀበሌ የ01ነዋሪ ወይዘሮ ምንትዋብ ካሳ ለኢዜአ እንደገለፁት 24 ነዋሪዎች በ2006 ተደራጅተው የመኖሪያ ቤት መስሪያ ቦታ እንዲሰጣቸው ለከተማው አስተዳደር ጥያቄ ማቅረባቸውን ይገልጻሉ።

በማህበራቸው አማካኝነት ከቆጠቡት ገንዘብ በተጨማሪ ከይዞታቸው ለሚነሱ አርሶ አደሮች የካሳ ክፍያ የተጠየቁትን 21 ሺህ ብር መክፈላቸውን አስታውሰዋል ።

የቤት መሥሪያ ቦታ ስላልተሰጣቸው በየወሩ ለቤት ኪራይ 1ሺህ 500 ብር ለመክፈል ተገድጄያለሁ ይላሉ ።

የቀበሌ 02 ነዋሪው አቶ ጉማታው መለሰ በበኩላቸው የቤት መስሪያ ቦታ ለማግኘት ከአምስት ዓመታት በፊት ተደራጅተው ጥያቄ ማቅረባቸውን ተናግረዋል ።

“የማህበሩ አባላት በየወሩ 500 ብር ስንቆጥብ ቆይተናል” ያሉት አቶ ጉማታው፤ ባለፈው ዓመት ቦታ ለማግኘት ተራ እንደደረሳቸው በተነገራቸው መሰረት ለካሳ ክፍያ የተጠየቁትን 21 ሺህ ብር መክፈላቸውን ተናግረዋል ።

“ዘንድሮም ከመጉላላት በስተቀር ቦታውን ባለማግኘቴ አቅሜን ካላገናዘበ የቤት ክፍያ መላቀቅ ተስኖኝ ተቸግሬያለሁ” ሲሉም ቅሬታቸውን ገልፀዋል ።

የዞኑ ቤቶች ልማትና ኮንስትራክሽን መምሪያ የከተማ መሬት ግብይት ባለሙያ አቶ አብዱረህማን ጌታነህ በዞኑ ስር በሚገኙ ከተሞች ከ2006 ጀምሮ በ2ሺህ ማህበራት የተደራጁ 40 ሺህ ነዋሪዎች የቤት መስሪያ ቦታ ጥያቄ ማቅረባቸውን አስታውሰዋል ።

“በቀረበው ጥያቄ መሰረት በ800 ማህበራት ለተደራጁ 15 ሺህ መምህራን፣ ሠራዊት ተመላሾች፣ ነዋሪዎችና የመንግስት ሰራተኞች ቦታ ተሰጥቷል” ብለዋል፡፡

ቀሪዎቹ በ1 ሺህ 200 ማህበራት የተደራጁ 25 ሺህ ነዋሪዎች ግን ቦታ እንዳላገኙ ተናግረዋል ።

የአመራር መቀያየርና ቁርጠኝነት ማነስ፣ የመሬት አቅርቦት እጥረት፣ በተደራጁ አባላት አለመስማማትና የደንብ ማስከበር ክፍተት ለነዋሪዎች ጥያቄ ፈጣን ምላሽ እንዳይሰጥ ያደረጉ ምክንያቶች ናቸው ይላሉ።

ሆኖም “ሐይቅን ጨምሮ በኮምቦልቻ ፣ ውጫሌ፣ ማሻና ወረኢሉ ከተሞች በ78 ማህበራት ለተደራጁ ነዋሪዎች የሚሰጥ በ540 ሄክታር መሬት ተዘጋጅቷል” ብለዋል።

ነዋሪዎች ለካሳ ክፍያ የከፈሉት ገንዘብ በባንክ ዝግ ሂሳብ መቀመጡን የገለጡት ባለሙያው፣እስከዚህ ወር መጨረሻ ድረስ ለነዋሪዎቹ የተዘጋጀላቸውን ቦታ እንደሚረከቡ አመልክተዋል ።

በዞኑ የተለያየ ደረጃ ያላቸው 100 ከተሞች መኖራቸው ታውቋል ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም