የኢትዮጵያ ግብርና ምግብና መጠጥ ቴክኖሎጂ ዓለም አቀፍ የንግድ ትርኢት ተከፈተ

86

አዲስ አበባ ግንቦት1/2011 በግብርና፣ ምግብና መጠጥ ማቀነባበር ላይ ትኩረቱን ያደረገው 3ኛው ዓለም አቀፍ የንግድ ትርኢት በአዲስ አበባ ሚሊኒየም አዳራሽ ተከፈተ።

ትርኢቱ የአገሪቱን የአግሮ ኢንደስትሪ ዘርፍ ለማጠናከር የሚያስችል የቴክኖሎጂ ሽግግርን ለመፍጠር እንደዚሁም የውጭ ኢንቨስትመንትን ለመሳብ እድል ይፈጥራል ተብሏል። 


በንግድ ትርኢቱ ላይ የግብርና ምርቶችን በፋብሪካ በማቀነባበር ለገበያ የሚያቀርቡ 152 የአገር ውስጥና የውጭ አገራት ኩባንያዎች ተሳትፈዋል።  

ከውጭ አገራት ተሳታፊዎች መካከል ጀርመን፣ ኔዘርላንድ፣ ቱርክ፣ ቻይና፣ ፈረንሳይና ጣልያን፣ ኦስትሪያ፣ ዴንማርክ፣ ህንድ፣ ማሌዥያ፣ ኮትዲቩዋር፣ ኬንያ፣ ደቡብ አፍሪካ፣ ሳዑዲ አረቢያ፣ አሜሪካና ሩሲያ ይገኙበታል።   

በኢትዮጵያ የንግድ ትርኢቱ መካሄድ የአገሪቱን የአግሮ ኢንደስትሪ ዘርፍ ለማጠናከር የሚያስችል የቴክኖሎጂና የእውቀት  ሽግግርን ለመፍጠር እንደዚሁም የውጭ ኢንቨስትመንትን ለመሳብና የወጪ ንግድን ለማስፋፋት የሚያግዝ  እድል ይፈጥራል ሲሉ የግብርናና እንስሳት ኃብት ሚኒስቴር ተወካይ አቶ አብዱልሰመድ አብዶ በዚሁ ወቅት ተናግረዋል።

የውጭ ኩባንያዎች ከግብርና ወደ ኢንዱስትሪ ሽግግር ለማድረግ እየተጋች ባለችው ኢትዮጵያ በአምራች ዘርፉ ምን ያህል አቅም እንዳላት የሚያዩበትና ቀጣይ ኢንቨስትመንት መዳራሻ ለማድረግ ሁኔታዎችን የሚያመቻቹበት ይሆናል ተብሎም እንደታመነበት አስታውቀዋል።   

በአገሪቷ የሚመረቱ የግብርና ምርቶችን የአገር ውስጥ ፍጆታን ከመሸፈን ባሻገር በስፋት ወደውጭ ለመላክ ጥረት ይተደረገ ነው ያሉት አቶ አብዱሰመድ ለዚህም መንግስት በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች የጀመራቸው የአግሮ ኢንዱስትሪ ፓርኮች ግንባታ ሥራ በመጠናቀቅ ላይ መሆኑን ተናግረዋል።  

የኢትዮጵያ የምግብ፣ መጠጥና መድሃኒት ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር አቶ ሰለሞን ታደለ በበኩላቸው ኢትዮጵያ ወደ ውጭ የምትልካቸው የግብርና ምርቶች እሴት የታከለባቸው እንዲሆኑና የቴክኖሎጂ ሽግግርን ለመፍጠር መሰል የንግድ ትርኢት አወንታዊ ሚና አለው ብለዋል። 

ከኢትዮጵያ ቡናን የመሳሰሉ የግብርና ምርቶችን በጥሬው የሚገዙ አገራት በዚህ የንግድ ትርኢት ላይ መሳተፋቸው ኩባንያዎች አገሪቷ በተጨባጭ ያላትን አቅም አይተው በኢትዮጵያ ኢንቨስት እንዲያደርጉ በር ይከፍታልም ሲሉ አብራርተዋል ።   

የግብርና ምርቶችን በቴክሎጂ በመታገዝ በጥራትና በጥንቃቄ የሚያሽጉ ኩባንያዎች ተሞክሮቸውን በዚህ የንግድ ትርኢት ላይ ይዘው ቀርበዋል።    

የኬሚካልና የኮንስትራክሽን ግብአቶች ኢንዱስትሪ ልማት ኢኒስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር አቶ ሳሙኤል ሀላላ፤ አገሪቷ ምርቶችን በጥራት ማሸግ ላይ ወደ ኋላ መቅረቷን ተናግረዋል።

በዚህ የንግድ ትርኢት ላይ ምርት ማሸግ ላይ የተሻለ አቅምና መሳሪያ ያላቸው ድርጅቶች በመሳተፋቸው ሰፊ ልምድ ይገኛል ብለዋል።     

በጀርመኑ የንግድ ትርኢት አዘጋጅ ፌር ትሬዲንግና ፕራና ፕሮሞሽን ኤቨንትስ በጋራ የተዘጋጀው የንግድ ትርኢቱ ከዛሬ ግንቦት 1 ቀን 2011 ዓም ጀምሮ ለሦስት ቀናት ይቆያል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም