የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማህበር እየሰጠ ያለው ሰብዓዊ ድጋፍ የሚበረታታ ነው- ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ

100

አዲስ አበባ ግንቦት 1/2011 የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማህበር በአገሪቱ የተለያዩ ክፍሎች በተፈጠረው ችግር ለተጎዱ ዜጎች እያቀረበ ያለው ሰብአዊ ድጋፍ የሚበረታታ ነው ሲሉ ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ ገለፁ።

የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል የበላይ ጠባቂ የሆኑት ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ይህንን የገለፁት የዓለም አቀፉ ቀይ መስቀል እና ቀይ ጨረቃ ቀን ዛሬ ሲከበር ባስተላለፉት መልዕክት ነው።

ፕሬዚዳንቷ የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማህበር ባለፉት ወራት በለተያዩ የአገሪቱ ክፍሎች በተከሰቱ ሰው ሰራሽና የተፈጥሮ ችግሮች ሳቢያ ለተጎዱና ለተፈናቀሉ ዜጎች እየሰጠ  ያለውን የህይወት አድን ተግባር አድንቀዋል።

ማህበሩ ባለፉት ሶስት ወራት ብቻ 40 ሚሊዮን ብር ወጪ በማድረግ ለተፈናቃዮች ሰብአዊ ድጋፍ ማድረጉን ፕሬዚዳንቷ ጠቅሰዋል።

በአሁኑ ወቅት የዓለም ለጋሽ አገራት የሚሰጡት ድጋፍ እየቀነሰ መምጣቱን የገለፁት ፕሬዚዳንቷ ማህበሩ የገቢ አቅሙን ዘላቂ ማድረግ እንዲቻለው በአገር ውስጥ ኃብት ማሰባሰብ ተግባር ላይ ጠንክሮ መስራት እንዳለበትም አሳስበዋል።

ኢትዮጵያዊያንም ለማህበሩ የሚሰጡትን ድጋፍ አጠናክረው እንዲቀጥሉ ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ጥሪ አስተላልፈዋል።

የማህበሩ ዋና ጸሃፊ ዶክተር መሸሻ ሸዋረጋ በበኩላቸው ህዝቡ ጉዳት ለደረሰባቸው ዜጎች እየሰጠ ያለው ድጋፍ የሚደነቅ ቢሆንም ካለው ችግር አንጻር ግን በቂ አይደለም ነው ያሉት።

በመሆኑም ማህበሩ የሚሰጠውን ሰብአዊ ድጋፍ ተደራሽ ማድረግ እንዲቻለው የህዝቡ የነቃ ተሳትፎ የበለጠ መጠናከር አለበት ሲሉም ገልፀዋል።

በኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት የተለያየ ሰብዓዊ እርዳታ የሚያስፈልጋቸው ዜጎች ቁጥር ከ8 ነጥብ 6 ሚሊዮን በላይ ሆኗል። ከዚህ ውስጥ ከ3 ሚሊዮን የሚሆኑት በአገሪቱ በተከሰቱ ግጭቶች የተፈናቀሉ መሆናቸውን ጠቁመዋል።

በበዓል አከባበሩ ላይ የተገኙት የሰላም ሚኒስትር ዴዔታ ወይዘሮ አልማዝ መኮንን በበኩላቸው በኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላም እንዲሰፍንና የዜጎችን ደህንነት ለማረጋገጥ ህዝቡ የአብሮነትና የመተሳሰብ ባህላዊ እሴቶቹን እንደገና ማደስ አለበት ብለዋል።

በአሁኑ ወቅት ተፈናቅለው በተለያዩ መጠለያዎች የሚኖሩትንና በሰው ሰራሽና የተፈጥሮ አደጋዎች የተጎዱትን መልሶ ለማቋቋም በሚደረገው እንቅስቃሴ መላው ህዝብ ጠንካራ ተሳትፎ እንዲያደርግም ጥሪ አስተላልፈዋል።

"ሰብዓዊነት ለሰላም" በሚል መሪ ሀሳብ የተዘጋጀው የዘንድሮ የዓለም አቀፍ የቀይ መስቀል እና የቀይ ጨረቃ ቀን በኢትዮጵያ ሲከበር ለ61ኛ ጊዜ ሲሆን በዓለም አቀፍ ደረጃ ደግሞ ለ72ኛ ጊዜ ነው።

የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማህበር 5 ነጥብ 5 ሚሊዮን አባላት ያሉት ሲሆን ከ40 ሺህ በላይ በጎ ፍቃደኞች አብረውት ይሰራሉ።  

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም