በድሬደዋ ሥራ ለሌላቸው ምሩቃን ወጣቶች የተገነባው የመለዋወጫ ማምረቻ ድርጅት ወደ ስራ ባለመግባቱ ቅሬታ ፈጥሯል

67
ድሬደዋ ግንቦት 28/2010 በድሬዳዋ አስተዳደር ሥራ ለሌላቸው ለከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ምሩቃን  ተብሎ የተገነባው የመለዋወጫ ማምረቻ  ድርጅት ወደ ስራ ባለመግባቱ ቅሬታ እንዳሳደረባቸው  አስተያየታቸውን የሰጡ ምሩቃን ወጣቶች ተናገሩ፡፡ የአስተዳደሩ የንግድ ኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት ቢሮ በበኩሉ  የመለዋወጫ ማምረቻ  ድርጅቱ ማሽን ስላልተሟላለት  በሙሉ አቅም ወደ ስራ ማስገባት እንዳልቻለ ገልጿል፡፡ በ2007ዓ.ም. በብረታ ብረትና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን /ሜቴክ/ በ47 ሚሊዮን ብር ወጪ የተገነባው ድርጅት  ከዩኒቨርሲቲና ከቴክኒክና ሙያ ተመርቀው ያለሥራ ለተቀመጡ 101 ወጣቶች ከባንክ ጋር በማስተሳሰር በረዥም ጊዜ ክፍያ ተጠቃሚና  ባለቤት እንዲሆኑ ማድረግ ዓላማ አድርጓል፡፡ ወጣቶቹ ለኢዜአ እንዳሉት መንግስት የተማረውን ወጣት ተጠቃሚ ለማድረግ ከፍተኛ በጀት መድቦ ድርጅቱን መገንባቱ የሚደገፍ ነው፡፡ ባለፉት ሁለት ዓመታት በሜቴክና በአስተዳደሩ የተለያዩ ሥልጠናዎች ያገኙና በፍጥነት ወደ ስራ እንደሚገቡ ቃል ቢገባላቸውም  እስካሁን ወደ ስራ ባለመግባቱ ቅሬታ አስድሮባቸዋል፡፡ ከወጣቶቹ መካከል  ሰለሞን ጌታሁን እንደተናገረው ሁሉንም ቅድመ ዝግጅት አጠናቀው  በሙሉ አቅም ወደ ስራ ለመግባት የጥሬ እቃ መግዣና የሥራ ማስኪያጃ ችግር አጋጥሟቸዋል። በተደጋጋሚ ለሚመለከተው አካል ያቀረቡአቸው ጥያቄ ምላሽ ባለማግኘቱ ወጣቶቹ ተስፋ ቆርጠዋል። "ሜቴክ ከቀረው የክፍያ ገንዘብ ሁሉት ሚሊዮን 500ሺህ ብር ወጣቶች ለጥሬ እቃና ለግብአት ማሟያ  እንዲጠቀሙበት ደብዳቤ ቢፅፍም እስካሁን ተግባራዊ የሆነ ነገር የለም  ብለዋል ወጣት ሰለሞን፡፡ በማርኬቲንግ የተመረቀው ወጣት በቀለ አማረ በበኩሉ በአስተዳደሩ የተገነባው ድርጅት  የነሱን ብቻ ሳይሆን የሌሎችም ወጣቶችን ህይወት የሚቀይር  መሆኑን ተናግሯል፡፡ " ለችግሩ ዘላቂ  መፍትሄ መስጠትና ወጣቱም በፍጥነት ወደ ማምረት በመግባት የሚጠበቅበትን ቀጣይ ብድር ከወዲሁ እንዲከፍል ማገዝ ይገባል"ብሏል፡፡ መንግስት የመለዋወጫ ማምረቻ  ድርጅቱ በከፍተኛ ወጪ እንዳስገነባው ሁሉ ፈጥኖ ወደ ስራ በማስገባት እንዲጠቀሙ ማመቻቸት እንዳለበት ያመለከተው ደግሞ  ሌላው ተመራቂ ወጣት ረመዳን መሐመድ ነው፡፡ የድሬዳዋ ንግድ ኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ ሙሣ ጣሃ በበኩላቸው  ቀደም ሲል ፕሮጀክቱን ያስገነባውም ሆነ ወጣቶችን መልምሎ ያደራጀው የቀድሞ ጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራዝ ልማት ኤጀንሲ እንደነበር ተናግረዋል፡፡ "ሜቴክ የተከላቸው ከፊሎቹ ማሽኖች መለዋወጫ ያልተሟላላቸው በመሆኑ ርክክብ አልተፈፀመም " ብለዋል፡፡ እንደ አቶ ሙሳ ገለጻ ሜቴክ ከቀረው የማሽነሪ 10 ሚሊዮን ብር ክፍያ ውስጥ ሁለት ሚለዮን 500ሺህ ብር ለጥሬ ዕቃ መግዣ የሚውል በመሆኑ ወጣቶቹ ከቢሮ ጋር የጋራ የባንክ ሂሳብ ተከፍቶላቸው ገንዘቡ በዚህ ሳምንት ይለቀቃል፡፡ የቀድሞው የጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዝ ልማት ኤጀንሲ የአሁኑ የከተማ ሥራ ዕድል ፈጠራ የምግብ ዋስትና ኤጀንሲ ሥራ አስኪያጅ አቶ ወጋየሁ ጋሻው " ሜቴክ ርክክቡ እስኪፈጸም ወጣቶቹ ወደ ስራ እንዲገቡ መፍቀዱ ወጣቶቹን ሙሉ በሙሉ እንዳይበታተኑ አግዟል" ብለዋል፡፡ ከሜቴክም ለመረከብ ጉዳዩ ወደ አስተዳደሩ ካቢኔ መመራቱን ጠቁመዋል፤  መሠረታዊ ጉዳይ ለወጣቶቹ የተቀናጀ ድጋፍ ፣ ክትትልና ቁጥጥር በማድረግ ውጤታማ እንዲሆኑ ማገዝ እንደሚገባም ጠቁመዋል፡፡
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም