ኮሚሽኑ 884 ሚሊዮን ብር በላይ ግምት ያላቸው ሕገ ወጥ ዕቃዎች መያዙን አስታወቀ

67

አዳማ ግንቦት 1/2011 ጉምሩክ ኮሚሽን ባለፉት ዘጠኝ ወራት 884 ሚሊዮን ብር በላይ ግምት ያላቸው ሕገ ወጥ(ኮንትሮባንድ) ዕቃዎች መያዙን ዛሬ ገለጸ።

የኮሚሽኑ ሕገ ወጥ እንቅስቅቃሴ የመቆጣጠር አቅም ወደ 33 በመቶ መድረሱም ተመልክቷል።

የጉምሩክ ኮሚሽነር አቶ ደበሌ ቃበታ ከፌዴራልና ከክልል የፍትህ አካላት ጋር ዛሬ በአዳማ ከተማ በተጀመረው መድረክ ላይ እንደተናገሩት በወጪና ገቢ ንግድ ላይ ያለውን ሕገ ወጥ እንቅስቃሴ ከመከላከል አንፃር የተሻለ አፈጻጸም ተመዝግቧል።

ኮሚሽኑ በ94 የመቆጣጠርያ ኬላዎች አዳዲስ አመራሮችና ባለሙያዎችን መመደቡን አመልክተዋል።


ሕገ ወጥ እንቅስቃሴ የሚበዛባቸውን ቦታዎች በጥናት በመለየት ተጨማሪ 39 መቆጣጠርያ ኬላዎቸን ለመክፈት እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

በኮሚሽኑ የሥነ ምግባር ችግር የታየባቸውና ከሕገ ወጦች ጋር ግንኙነት ያላቸው ተብለው የተጠረጠሩ አመራሮችና ሠራተኛችን የማጽዳት ስራ መሰራቱን የገለጹት ደግሞ የኮሚሸኑ የህግ ተገዢነት ዘርፍ ዳይሬክተር አቶ ሙሉጌታ በየነ ናቸው።

ኮሚሽኑ ባለፈው ዓመት ሕገ ወጥ ንግድን የመከላከል አቅሙ 16 በመቶ እንደነበር ያመለከቱት ዳይሬክተሩ፣ ዘንድሮ  አሰራሩንና አደረጃጀቱን በማስተካከል አቅሙን ወደ 33 በመቶ ማሳደጉን አመልክተዋል።

በዚህም ባለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ከነበረው  አፈጻጸም ብልጫ ያለው ገቢ መደረጉን ተናግረዋል።

መድረኩ የፍትህ አካላት የህግ አስከባሪዎች በዓዋጅ ቁጥር 85/2006 ላይ ግንዛቤያቸው እንዲሰፉና ለተግባራዊነቱ እንዲረባረቡ ለማድረግ ታስቦ መዘጋጀቱን ጠቁመዋል።ሕገ ወጥ ንግድ እየተበራከተ በመምጣቱ በአገር ፖለቲካና ኢኮኖሚ ያለመረጋጋት ምክንያት መሆኑን የገለጹት ደግሞ የኦሮሚያ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዘዳንት አቶ ደሳ ቡልቻ ናቸው ።

በሕገ ወጥ ንግድ የሚሰማሩ ግለሰቦች በሕግ እንዲዳኙና ለዓዋጁ ተፈፃሚነት እንደሚሰሩ የመድረኩ አንዳንድ ተሳታፊዎች ተናግረዋል።

ኮሚሽኑ በቅርቡ የጉምሩክ ፖሊስን በሥሩ ማደራጀቱ ይታወሳል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም