የቀድሞ የሰገን ህዝቦች ዞን አካባቢን ለማረጋጋት ኮማንድ ፖስት ተቋቋመ - የደቡብ ክልል ሰላምና ጸጥታ ቢሮ

107

ግንቦት1/2011 በደቡብ ክልል በቀድሞው ሰገን ህዝቦች ዞን አካባቢ እየታየ ያለውን የጸጥታ ችግር ለመፍታት አካባቢው ለአንድ ወር በኮማንድ ፖስት ስር እንዲቆይ መደረጉን የክልሉ ሰላምና ጸጥታ ቢሮ አስታወቀ።

የቢሮው ኃላፊ አቶ አንድነት አሸናፊ ዛሬ ለኢዜአ እንደገለጹት በቀድሞው የሰገን ህዝቦች አካባቢ ዞን በአሁኑ የኮንሶ ዞንና የአማሮ ቡርጂ ደራሼ ኧሌና ሰገን ወረዳዎች በዜጎች ላይ እየደረሰ ያለውን ጥቃት ለማስቆም ኮማንድ ፖስቱ ተቋቁሟል።

በነዚህ አካባቢዎች በተደራጁ ህገወጥ ሀይሎች በሚደርስባቸው ጥቃት ምክንያት በተለያዩ የገጠር ቀበሌዎች ከፍተኛ ቁጥር ያለው ነዋሪ ከቀየው መፈናቀልና ጉዳት እየደረሰበት መሆኑን ገልጸዋል።

በአጎራባች ኦሮሚያ ክልል ምዕራብና ምስራቅ ጉጂ ዞን ህገ-ወጥ ታጣቂዎች የሚያደርሱትን ጥቃት ለማስቆም የመከላከያ ሰራዊት በተሰጠው ግዳጅ መሰረት ህገ-ወጥ ማሰልጠኛ ካምፖችንና ጥቃት አድራሾችን የማጽዳት ስራ እየተሰራ እንደሚገኝም ጠቁመዋል።

ይሁን እንጂ ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ የመዋቅር ጥያቄን መሰረት ያደረገና የኔን ሀሳብ የሚደግፍና የማይደግፍ በሚል በተለያዩ ቀበሌዎች በተደረገ ጥቃት በአማሮ ወረዳ ቡኒቲ ቀበሌ በሰገን ሀይሎታ ቀበሌ በደራሼ ጋቶ ቀበሌ ቁጥሩ በርካታ የሆነ ነዋሪ መፈናቀሉንና መሞቱን ገልጸዋል።

“እነዚህ ህገ-ወጥ አካላት በርካታ የነፍስ ወከፍና የቡድን መሳሪያዎችን ታጥቀው በአካባቢው እያደረሱ ያሉትን ጥቃት ማስቆምና ሰላምን ማስፈን ዋና ስራው ያደረገው ኮማንድ ፖስት በአንድወር ቆይታው ህገ-ወጥ መሳሪያዎችን ማስፈታት ተፈናቃዮችን ወደ ቦታቸው መመለስ የፈረሱና የተቃጠሉ ቤቶችን የመጠገን ስራ ይሰራል” ብለዋል።

ከዚህ በተጨማሪም የህዝብ ለህዝብ ግንኙነቱን ለማጠናከር የማወያየትና ከህዝብ ጋር በመሆን ህገ-ወጦችን በመያዝ ለህግ ለማቅረብ እንደሚሰራም የቢሮ ሀላፊው ገልጸዋል።

በዚህም መሰረት ኮማንድ ፖስቱ በተቋቋመበት የኮንሶ ዞን የአማሮ ቡርጂ ደራሼ ሰገን ኧሌ ወረዳዎችና ከተሞች ለአንድ ወር የሚቆይ ክልከላዎችን ደንግጓል።

አካባቢዎቹ በአብዛኛው የገጠር ቀበሌዎች በመሆናቸው ከምሽቱ አንድ ሰዓት ጀምሮ የሚደረግ ተገቢ ያለሆነ እንቅስቃሴ ከኮማንድ ፖስቱ እውቅና ውጪ የሚደረግ ስብሰባ የጦር መሳሪያ ይዞ መገኘት ትንኮሳ ማድረግ መንገድ መዝጋት ሰላማዊ ሰልፍ ማድረግ መከልከሉን አስታውቀዋል።

ህብረተሰቡ በአካባቢው ያለውን ማንኛውንም እንቅስቃሴ በመከታተል ጥርጣሬ ሲያድርበት ለኮማንድ ፖስቱ ጥቆማ እንዲሰጥ አቶ አንድነት አሳስበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም