የቦረና ዞን ነዋሪዎች የሕዝቦችን ትስስር ለማላላት የሚንቀሳቀሱ የጥፋት ኃይሎችን በጋራ እንታገላለን አሉ

66

ነጌሌግንቦት 1/2011 በአብሮነት፣ በመቻቻልና መከባበር ለዘመናት የቆየውን የሕዝቦችን ትስስር ለማላላት የሚንቀሳቀሱ የጥፋት ኃይሎችን በጋራ እንደሚታገሉ የቦረና ዞን ነዋሪዎች ገለጹ፡፡

ከዞኑ 14 ወረዳዎችና ከያቤሎ ከተማ የተውጣጡ ከ500 በላይ ብሄር /ብሄረሰቦች የወንድማማችነትና የአንደነት መድረክ በያቤሎ ከተማ ተካሂዷል፡፡

ነዋሪዎቹ በከተማው ባካሄዱት መድረክ እንዳመለከቱት ትውልዶችን የተሸጋገረውን የብሄር/ብሄረሰቦች የአብሮነት ለመነጣጠል የሚደረገው እንቅስቃሴ አጥብቀው ይታገላሉ።

የያቤሎ ከተማ ነዋሪው የአገር ሽማግሌ አቶ ሁሴን መሐመድ በጋብቻና በደም የተሳሰረ አንድነት ያላቸውን ብሄር ፣ብሄረሰቦች ለመለያየት ጥረት የሚያደርጉ ወገኖች ከእኩይ ድርጊት ሊተቃቡ ይገባል ብለዋል።

አልፎ አልፎ የሚነሱ አለመግባባቶች በድርድርና በውይይት እንዲፈቱ ያሳሰቡት አስተያየት ሰጪው፤በዚህ ካልተሳካ ጉዳዩ በህግ ብቻ እንዲታይ ጠይቀዋል፡፡

የህግ የበላይነት እንዲከበር ጥፋተኞችን ማጋለጥ፣ማስተማርና ማንቃት የአገር ሽማግሌዎች፣ የአባገዳዎችና የሃይማኖት አባቶች ድርሻ መሆን ይገባዋል ብለዋል፡፡

የሞያሌ ወረዳ ነዋሪ አቶ ጎዳና ኩሉ አብሮነትን ለማጥፋት ህዝብን ከህዝብ በማጋጨት የፖለቲካ ትርፍ ለማግኘት የሚመክሩ ኃይሎችም ሊያስቡበት እንደሚገባ ጠይቀዋል፡፡

ከተለያዩ ብሄር ብሄረሰቦች ጋር በፍቅር በመቻቻልና በመከባበር አብሮ የመኖር ልምድ ያለው በተለይ የአሮሞ ህዝብ ባለፉት ዓመታት ከተፈጠሩ ሁከትና ብጥብጥ መማራቸውን ይገልጻሉ፡፡

ለዘመናዊ ሕግ መሠረት የጣለውን የገዳ ባህላዊ ሥርዓት ባለቤት የኦሮሞን ህዝብ ከሌሎች ከብሄር ብሄረሰቦች ጋር ለማጋጨት የተደረገው ሙከራ እንዳልተሳካ አመልክተዋል፡፡

በአገሪቱ ሰላምና ልማት ለማሰቀጠልም  መንግሥት የህግ የበላይነትን በማስከበር ኃላፊነቱን እንዲወጣም ጠይቀዋል፡፡

የተልተሌ ወረዳ ነዋሪ አቶ አቶ ማርቆስ ጉርጉሮ በህዝብ ውስጥ ተደብቀው እርስ በርስ ለማጋጨት የሚሰሩ አካላትን ድርሻችንን እንወጣለን ብለዋል፡፡

መንግሥትም የህግ የበላይነትን በማስከበር ለዘመናት የኖረው የብሄር/ብሄረሰቦች ወንድማማችነት መቻቻልና መከባር በህገ ወጦች ከሚደርስበት ጉዳት መከላከል እንዳለበት አሳስበዋል፡፡

በአንዳንድ አካባቢዎች አሁን እየታየ ያለው ሞትና መፈናቀል በጥቂት የፖለቲካ ትርፍ ፈላጊዎች በሚቆሰቁሱት የብጥብጥ አጀንዳ የተፈጠረ እንጂ፤ የብሄር/ ብሄረሰቦች ጠብ እንዳልሆነ ጠቁመዋል፡፡

የቦረና ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ዴንጌ ቦሩ መንግሥት የህግ የበላይነትን ለማስከበር የህዝብ ድጋፍና ትብብር ያስፈልጋል ብለዋል፡፡

ጥፋተኞችን ማጋለጥ ሕገወጠችን ደግሞ አስተምሮና መክሮ መመለስ ቅድሚያ መስጠት እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል፡፡

አባገዳዎች፣ የሃይማኖት አባቶችና የአገር ሽማግሌዎች ህዝብን በማስተማርና በማንቃት የጠፋውን ሰላም ለመመለስ የጥፋት ኃይሎችን ከህዝብ ለመነጠል እያደረጉ ያለው ጥረት እንዲያጠናከሩም ጠይቀዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም