በማምቡክና አካባቢው ግጭት ተጠርጥረው የተያዙ ሰዎች ቁጥር 62 ደርሷል

118

አሶሳ ግንቦት 1/2011 በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል መተከል ዞን በማምቡክና አካባቢው ግጭት ተጠርጥረው በቁጥጥር ስር የዋሉ ሰዎች ቁጥር 62 መድረሱን ፖሊስ አስታወቀ፡፡

የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር መሃመድ ሀምደኒል ለኢዜአ እንዳሉት ማምቡክና አካባቢው ከጸጥታ ችግር ወጥተው በአሁኑ ወቅት ወደ ቀደመ መረጋጋት ተመልሰዋል፡፡

“በግጭቱ ምክንያት ተቋርጦ እና ተስተጓጉሎ የነበረው የአሶሳ- ግልገል በለስ፣ የግለገል በለስ- ማምቡክ፣ የግልገል በለስ-ፓዌ-ጃዊ-ማንኩሽና እና ሌሎችም ከተሞች የህዝብ ትራንስፖርት ትናንት እንደገና ተጀምሯል” ብለዋል፡፡

በፌዴራል እና በክልል ፖሊስ የተደራጀው ግጭቱን የሚመረምረው ቡድን ስራውን አጠናክሮ መቀጠሉን ኮሚሽነር መሃመድ ጠቅሰዋል፡፡

እስከ አሁን በማምቡክና አካባቢው ግጭት ተጠርጥረው የተያዙ ሰዎች ቁጥር 50 ሲደርስ  በጃዊ ግጭት ደግሞ ሌሎች 12 ሰዎች መያዛቸውን ተናግረዋል፡፡

ተጠርጣሪዎቹ በመተከል ዞን ግልገል በለስ ከተማ እና በዳንጉር ወረዳ ማምቡክ ከተማ እስር ቤቶች እንደሚገኙ ጠቅሰዋል፡፡

በተጠርጣሪዎች ላይ ማስረጃ የማሰባሰብ ሥራው መቀጠሉንም አስታውቀዋል፡፡

በቅርቡ የምርመራ ቡድኑ 200 የሚጠጉ የቀስት ደጋን ከነመወርወሪያው፣ ገጀራ እና መጥረቢያ በቁጥጥር ስር ማዋሉን ኮሚሽነሩ ጨምረው ገልጸዋል፡፡

በማምቡክና አካባቢው ግጭት የ21 ሰዎች ህይወት እንዳለፈ መገለጹ ይታወሳል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም