በቦሎሶ ሶሬ ወረዳ በደረሰ የተሽከረካሪ አደጋ አንድ ሰው ሲሞት፤ 12 ቆሰሉ

72

ሶዶሚያዝያ 30/ 2011በወላይታ ዞን ቦሎሶ ሶሬ ወረዳ በደረሰ የተሽከርካሪ አደጋ የአንድ ሰው ህይወት ሲያልፍ በ12 ሰዎች ላይ ከባድና ቀላል የአካል ጉዳት መድረሱን ፖሊስ አስታወቀ።

አደጋው የደረሰው የሠሌዳ ቁጥር ኮድ 3-13474 ደቡብ ሕዝቦች የሆነ አነስተኛ የህዝብ ማመላለሻ ተሽከርካሪ ትናንት መንገደኞችን አሳፍሮ ከሶዶ ወደ አረካ ከተማ በመጓዝ ላይ እንዳለ ዶላ ቀበሌ በመገልበጡ ነው ።

የወረዳው የትራፊክ አደጋ መከላከልና ቁጥጥር ዋና የስራ ሂደት አስተባባሪ ዋና ሳጂን አዳነ ተስፋዬ ለኢዜአ እንደገለጹት ተሽከርካሪው በፍጥነት በመጓዘ ላይ እያለ ባጋጠመው የፊት የቀኝ ጎማ የመተንፈስ ችግር ተገልብጦ አደጋው ተከስቷል።

በአደጋው የአንድ ተሳፋሪ ህይወት ወዲያውኑ ሲያልፍ፣አሽከርካሪና ረዳቱን ጨምሮ ሰባት ሰዎች ከባድ የአካል ጉዳት ደርሶባቸዋል ብለዋል።

ሌሎች አምስት ተሳፋሪዎች ደግሞ ቀላል የአካል ጉዳት እንዳጋጠማቸው አስተባባሪው አመልክተዋል።

የሟች አስከሬን ለቤተሰቦቹ መሰጠቱንም ዋና ሳጂን አዳነ አስታውቀዋል።

በአደጋው ከባድ የአካል ጉዳት የደረሰባቸው በወላይታ ሶዶ ክርስቲያን ሆስፒታል የህክምና እርዳታ እየተደረገላቸው መሆኑንም ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም