በአፋርና ሱማሌ ክልሎች አዋሳኝ የተፈጠረውን ግጭት በውይይት ለመፍታት መሪዎቹ ተስማሙ

106

ሚያዝያ 30/2011 የአፋርና ሱማሌ ክልሎቹ በአዋሳኝ ቦታ ላይ የተከሰተውን ግጭትና ወደፊት ሊከሰቱ የሚችሉ ችግሮችን በውይይት ፈተው ሰላምን ለማረጋገጥ የጋራ አቋም ላይ መድረሳቸውን የክልሎቹ መሪዎች አስታወቁ።

በሱማሌና አፋር ክልሎች አዋሳኝ ቦታ ላይ የተፈጠረውን ግጭት አስመልክቶ የሰላም ሚኒስቴር የክልሎቹን ርዕሰ መስተዳድሮች ዛሬ አወያይቷል።

የሰላም ሚኒስትር ወይዘሮ ሙፈሪያት ከሚል ከውይይቱ በኋላ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ በክልሎቹ አዋሳኝ ቦታ ላይ የተፈጠረው ግጭት በማንኛውም አካባቢ ሊፈጠር ይችላል። ይህ ሁኔታ የተከሰተ ቢሆንም የሁለቱን ክልሎች ህዝቦች ተጠቃሚ በሚያደርግ መልኩ በውይይት ለመፍታት አመራር አባለቱ ቁርጠኛ ናቸው።

በውይይቱም የክልሎቹ አመራር አባላት በጋራና በሰላማዊ መንገድ ዘላቂ መፍትሄ ለማምጣት መግባባት ላይ የደረሱ መሆኑን አመልክተው፤ ለዚህም ፌዴራል መንግስት የሚጠበቅበትን ሚና እንደሚወጣም ሚኒስትሯ ተናግረዋል።

የሱማሌ ክልላዊ መንግስት ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ሙስጦፌ ሙሃመድ በበኩላቸው እንደገለጹት፤ ግጭቱን አስመልክቶ ሰሞንኑን በተለያዩ ማህበራዊ ሚዲያዎች የሚናፈሱት መረጃዎች የተጋነኑ ናቸው። ችግሩ ቀላልና በውይይት የሚፈታ ነው።

የሱማሌ ህዝብ ከአፋር ህዝብ ጋር "በድንበር፣ በባህልና በተለያዩ ማህበራዊ ጉዳዮች የተሳሰር" ነው ያሉት ምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ፤ የሁለቱን ክልሎች ህዝቦች ሰላም ለመጠበቅና ችግሮችን በውይይት ለመፍታት "ቁርጠኛ ነን" ሲሉ ነው የገለጹት።

የአፋር ክልላዊ መንግስት ርዕሰ መስተዳድር አቶ አወል አርባ፤ ለተፈጠረው ግጭትም ሆነ ለሁለቱ ክልሎች ህዝቦች ቀጣይ አብሮነት መጎልበት ትልቁ መፍትሄ "የህዝብ ለህዝብ ትስስራችንን ማጠናከር ነው" ብለዋል።

በተያያዘ ዜናም የሰላም ሚኒስቴር ከኢትዮጵያ ብሄራዊ እርቅ ኮሚሽን ጋር ሰላምና መረጋጋትን በተመለከቱ ጉዳዮች ላይ መክሯል።

በውይይታቸው ላይ ኮሚሽኑ ወደ ስራ ለመግባት "ዝግጅቱን እየጨረሰ መሆኑን አውቀናል" ያሉት ሚኒስትሯ፤ ኮሚሽኑ ጋር አብሮ ለመስራት የሚያስችሉና በሰላም ሚኒስቴር በኩል መዘጋጀት ያለባቸው የአሰራርና የህግ ማዕቀፍ ጉዳዮችም እየተሰሩ መሆናቸውን ገልፀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም