የአንድነትና የአብሮነት እሴት በጸረ ሠላም ኃይሎች እንደማይናድ የምዕራብ ሐረርጌና የምዕራብ ወለጋ ዞኖች ነዋሪዎች ገለጹ

64

ጭሮ/ነቀምቴ (ረያ) ሚያዝያ 30/ 2011ለትውልዶች የገነቡት የአንድነትና የአብሮነት እሴት በጸረ ሠላም ኃይሎች እንደማይናድ የምዕራብ ሐረርጌና የምዕራብ ወለጋ ዞኖች የብሔር፡ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ተወካዮች አረጋገጡ። 

የዞኖቹ ተወካዮች ዛሬ በጭሮና በነቀምቴ ከተሞች ባካሄዷቸው ኮንፍረንሶች እንዳመለከቱት ትውልዶችን የተሸጋገረውን አንድነትና ኅብረታቸውን ለመሸርሸር እየተደረጉ ያሉትን እኩይ ተግባራት በመታገል ለጋራ ሰላማቸውና ዕድገታቸው ይጥራሉ።

በጭሮ መድረክ ላይ ከተሳተፉት መካከል አቶ አማረ ሺፈራው የተባሉ የአማራ ብሄር ተወላጅ  ለዘመናት በፍቅርና በመከባበር እንዲሁም በመቻቻል አብሮ የኖሩበትን እሴቶች  በማጎልበት ለአገሪቷ ሰላምና ብልጽግና  ለመስራት እንተጋለን ብለዋል።

በቅርቡ በአገሪቷ ተከስቶ የነበረው ግጭትና መፈናቀልም የፖለቲካ ቁማርተኞች እንጂ፤ የህዝቦች መሠረታዊ አጀንዳ እንዳልሆነ ገልጸዋል።

አቶ ሸሪፍ ገለታ የሀብሮ ወረዳ ነዋሪ የኦሮሞ ብሄር ተወላጅ በበኩላቸው ከበርካታ ብሄር ብሄረሰቦች ተወላጆች ጋር  ደስታና ኅዘንን በጋራ ያሳለፍን፤ለዘመናት ያልተለያየን በጋብቻ ተሳስረን ደም ለደም የተቀላቀልን ህዝቦች በመሆናችን የጋራ እሴቶቻችንን አጠናክረን ታሪክ እንሰራለን ብለዋል።

ከዚህም አልፎ የአገርን ሉአላዊነትን ለማሰከበር የተሰለፍን በመሆናችን በፖለቲካ ቁማርተኞች የመከፋፈልና የመለያየት አጀንዳ አንለያየንም ሲሉ  ተናግረዋል።

የምዕራብ ሐረረጌ ዞን ዋና አሰተዳዳሪ አቶ አብዱረህማን አብደላ በበኩላቸው እንደተናገሩት ባለፉት ሶስት አመታት ግጭትና ትርምስ ለመፍጠር የሚጥሩ የጥፋት ኃይሎች  እንደነበሩ  አስታውሰው፣በፍቅርና በመተሳሰብ አብሮ የኖረው ሕዝብ  የጋራ እሴቶቹን በማጎልበት እንዳሳፈራቸው ገልጸዋል።

የድሎችን ቀጣይነትና  ዘላቂነት ለማረጋገጥ  እንዲሆን በዞኑ የሚገኙ ብሄር ፣ብሄረሰቦች ድርሻቸውን እንዲወጡም ጠይቀዋል።

በተመሳሳይ በምዕራብ ወለጋ  ከ20 ወረዳዎችና ከሦስት  የከተማ አስተዳደሮች የተውጣጡ ከአንድ ሺህ በላይ የብሔር፣ብሔረሰቦች ተወካዮች የሰላም ኮንፍረንስ በጊምቢና መንዲ ከተሞች ተካሂዷል።

ከኮንፍረንሱ ተሳታፊዎች መካከል የመነ ሲቡ ወረዳ የሐረዌ ደንቢ ቀበሌ ነዋሪ አባ ገዳ ቀጄላ ደንበል በሰጡት አስተያየት የኦሮሞ ሕዝብ ለብዙ ሺህ ዓመታት በአገሪቱ ከሚኖሩ ብሔር ብሄረሰቦች ጋር አንድነቱን ጠብቆ በመቻቻል፣በመረዳዳት፣በመደጋገፍና በመፈቃቀር የኖረ ሕዝብ እንጂ ፣ገፊ ሕዝብ አለመሆኑን ገልጸዋል።

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ሕዝቡን ለማለያየትና የኦሮሞን ሕዝብ መልካም እሴት ለማበላሸት የሚጥሩ የፖለቲካ ነጋዴዎች ሕዝቡን ሰላም በመንሳት አብሮነቱን በማዳከምና የፖለቲካ ትርፍ ለማግኘት ግጭቶችን እያባባሱ መገኘታቸውንም አስረድተዋል።

የባምባሲ ከተማ 02 ቀበሌ ነዋሪው የበርታ ብሔረሰብ ተወላጅ አቶ ጃፋር መርቀኒ በበኩላቸው የኦሮሞና የብርታ ሕዝቦች የተጋቡና የተዋለዱ ለበርካታ ዓመታት በሰላም አብረው የኖሩ ሕዝቦች መሆናቸውን ገልጸው፣ አንድነታቸው በጸረ ሰላም ኃይሎች የማይናድ ሕዝቦች ናቸው ብለዋል

የአሶሳ ዞን የኦዳ ቡልዲጂሉ ወረዳ ፖሊስ አዛዥ ሳጂን አብዱል ማሩፍ መሃዲ በበኩላቸው የሕዝቦቹን አንድነት የማይፈልጉ ኪራይ ሰብሳቢዎች የኦሮሞንና የበርታን ሕዝቦችን አንድነትና ወንድማማችነት ማደናቀፍ እንደማይችሉ ገልጸው፣ ሁለቱ ሕዝቦች እጅና ጓንት ሆነው በሰላም በመዋደድና በመፈቃቀር አብረው እንደሚኖሩ ተናግረዋል።

የምዕራብ ወለጋ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ገመቺስ ተመስጌን በበኩላቸው በዞኑ የሚኖሩ ብሔር፣ብሔረሰቦችን በየጊዜው አዳዲስ አጀንዳ በመፍጠር ሕዝቦችን ለማናቆር የሚያናፍሱትን አፍራሽ ፕሮፖጋንዳ ነቅቶ በመጠበቅ ለውጡ ማስቀጠልና እንድነቱን እንዲያጠናክር አሳስበዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም