ህብረቱ ተፈናቃዮችን መልሶ ለማቋቋምና ለአደጋ ስጋት መከላከል ድጋፍ አደረገ

67

ሚያዝያ 30/ 2011 የአውሮፓ ህብረት ተፈናቃዮችን መልሶ ለማቋቋምና ለአደጋ ስጋት መከላከል ከ30 ሚሊዮን በላይ ዮሮ ለኢትዮጵያ ድጋፍ አደረገ።

ስምምነቱን የተፈራረሙት የገንዘብ ሚኒስትር ዴኤታ አቶ አድማሱ ነበበ እና በኢትዮጵያ የአውሮፓ ህብረት ተወካይ ሚስተር ኤሪክ ሃበርስ ናቸው።

ድጋፉየ33 ነጥብ 5 ሚሊዮን ዮሮ ወይም የአንድ ነጥብ 85 ቢሊዮን ብር ሲሆን በተለያዩ አካባቢዎች የሚያጋጥመውን የአደጋ ስጋት ለመከላከልና ተፈናቃዮችን መልሶ ለማቋቋም የሚውል ነው ተብሏል።

የገንዘብ ሚኒስትር ዴኤታው አቶ አድማሱ በዚሁ ጊዜ እንዳሉት የአውሮፓ ህብረት የኢትዮጵያ የረጅም ጊዜ የልማት አጋር በመሆን በተለያዩ ዘርፎች ድጋፍ እያደረገ ነው።

ዛሬ የተደረገው ድጋፍም መንግስት እያከናወነ ያለውን የአደጋ መከላከል ስራ የሚያግዝና በተለያዩ ምክንያቶች ከቤት ንብረታቸው የተፈናቀሉ ዜጎችን መልሶ ለማቋቋም የሚውል ነው።

በአየር ንብረት መዛባትና በተለያዩ ሰው ሰራሽ ችግሮች ለሚከሰቱ አደጋዎች አፋጣኝ ሰብዓዊ ድጋፍ ለማድረግ እንደሚያግዝም ተናግረዋል።

መንግስት የአደጋ ስጋትን ለመቀነስና ለመከላከል ፖሊሲና ስትራቴጂ ነድፎ የተለያዩ ስራዎችን እየሰራ መሆኑንም ሚኒስትር ዴኤታው አስረድተዋል።

ድጋፉ በተለይ የአገር ውስጥ ተፈናቃዮዎችን መልሶ ለማቋቋምና በተለያዩ ክልሎች እስከ ወረዳ ድረስ የአደጋ ስጋቶችን አስቀድሞ ለመከላከል ያግዛል ብለዋል።

ኢትዮጵያ የአውሮፓ ህብረት ተወካይ ሚስተር ኤሪክ ሃበርስ በበኩላቸው የአለም ስጋት በሆነው የአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት የሚመጡ ሰው ሰራሽ አደጋዎችን አስቀድሞ መከላከል ወሳኝ መሆኑን ገልጸው፤ ህብረቱ ኢትዮጵያ የአደጋ ስጋት ለመከላከልና በስራ ዕድል ፈጠራ ላይ ለምታከናውናቸው ስራዎች ድጋፍን እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም