ኢትዮጵያ ባለፈው አንድ አመት አስደናቂ ስኬት አስመዝግባለች- አምባሳደር ማይክል ራይኔር

76

ሚያዝያ 30/ 2011 በአገሪቷ ቀጥተኛ የውጭ ኢንቨስትመንት ፍሰት በ 10 በመቶ መጨመሩንና ዓለም አቀፉ የንግድ ማህበረሰብም በኢትዮጵያ ያለውን የፖለቲካና የኢኮኖሚ ማሻሻያ መገንዘቡን አምባሳደሩ ጠቅሰዋል።

ኢትዮጵያ የህግ የበላይነትን ለማስክበር የተለያዩ ማሻሻያዎችን እያደረገች ሲሆን፣የጸረ ሽብር አዋጅ እና የበጎ አድራጎት ማህበራት ህግ ማሻሻያዎች የዚህ ማሳያ ናቸው ብለዋል።

አምባሳደሩ አክለውም አሜሪካ በለውጥ ጅማሮ ላይ የገጠማት አይነት ችግር ኢትዮጵያም አሁን ላይ መጋፈጧን አልሸሸጉም።

ብዙ ኢትዮጵያውያን አገሪቷ እየሄደችበት ያለው መንገድ አስቸጋሪ መስሎ ይታያቸዋል ያሉት አምባሳደሩ፤ በተለይ መሰረታዊ ጥያቄያቸው የመንግስት አስተዳደርና መዋቅር ውጤታማነት ላይ ጥቂቶች ጠንከር ያሉ ጉዳዮችን ያነሳሉ ብለዋል።

አንዳንዶች የዲሞክራሲ ጭላንጭሉ አደጋን ተጋፍጦ በሂደት ውጤታማ ይሆናል ከማለት ይልቅ ለውጡ ፈጣንና ቀላል ላይሆን እንደሚችል በማሰብ ሌላ አካል ስልጣኑን በመቆጣጠር በአገሪቱ ልማት ላይ ውሳኔ መስጠት አለበት ይላሉ ብለዋል፤ ያም ሆኖ ኢትዮጵያውያን ራሳቸውን መምራት ያለባቸው ራሳቸው ናቸው በማለትም መክረዋል።

ኢትዮጵያ በታሪኳ ያጋጠማትን ይህንን እውነታ ተቀብለው መወሰን ያለባቸው ህዝቦቿ ብቻ ናቸው ሲሉም አምባሳደሩ ተናግረዋል።

አሜሪካንን የመሰረቱት ቀዳሚ አባቶቻችን ከ243 ዓመት በፊት ተመሳሳይ አጋጣሚ ደርሶባቸው እንደነበር በማውሳት።

"የኢትዮጵያ ህዝብ መጻኢ ተስፋ የለመለመ መሆኑ ይታየኛል" ያሉት አምባሳደሩ፤ ኢትዮጵያውያን በዚህ ሁኔታ በመበረታታት መጻኢ እድላቸውን ራሳቸው መወሰን አለባቸው፤ አገሪቷም የበለጠ ጠንካራ፣ ንቁና ስኬታማ ጊዜ እንዲኖራት የሚያደርገው ውሳኔ የህዝቦቿ ነው ብለዋል።

ኢትዮጵያውያን ብዝሃ ማንነታቸውን በመጠቀም ከመለያየት ይልቅ አንድ ላይ ማበር አለባቸው ያሉት አምባሳደሩ፤ አንዱ የሚፈለገውን ሌላው በተመሳሳይ እንደሚፈልገው በማወቅ ልዩነትን ውበት በማድረግ ለብልጽግና በጋራ መትጋት ይገባልም ብለዋል።

አማራጭን፣መቻቻልን፣ ብልጽግናን፣ ሰላምን፣ ነፃነትንና አክብሮትን ሁሉም ለሁሉም መስጠት አለበት ሲሉ መክረዋል።

እነዚህን እሴቶች የጋራ መደላድል በማድረግ ለግንባታ የሚረዳ ድንቅ መሰረት ማስቀመጥ እንደሚቻል የገለጹት አምባሳደር ራይኔር፣ እኔ እና አሜሪካ እንደምናምነው ኢትዮጵያ ሁሉም የሚጓጓለትን ቤት ለመስራት የሚረዳትን መሰረት ማስቀመጥ ትችላለች ብለዋል።

የአሜሪካ መንግሰትና ህዝብ ኢትዮጵያ የጋራ ቤቷን ለመገንባት የምታደርገውን ጥረት በቁርጠኝነት ይደግፋሉ ሲሉም ገልጸዋል።

የኢትዮጵያን መንግስት፣ ተቋማትንና የህዝብን አቅም በመገንባት ኢትዮጵያውያን የሚመኟትን አገር ለመገንባት እና በለውጥ ጉዞው ላይ የተጋረጠውን መሰናክል ለማስወገድ የሚረዳ ድጋፍ ለመስጠትም ቁርጠኛ ነን ሲሉም አምባሳደሩ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም