በግንባታው ዘርፍ ለተሰማሩ 200 ባለሙያዎች የአቅም ግንባታ ስልጠና እየተሰጠ ነው

65


መቐለ ሚያዝያ 29 /2011 በኢትዮጵያ በግንባታው ዘርፍ ለተሰማሩ 200 ባለሙያዎች የተሳተፉበት የአቅም ግንባታ ስልጠና ዛሬ በመቀሌ ከተማ ተጀምሯል።

በሥልጠናው ሁለት የከተማ አስተዳደሮችን ጨምሮ ዘጠኙ ክልሎች የሚገኙ የሥራ ተቋራጮች፣አማካሪዎችና የምህንድስና ባለሙያዎች በመሳተፍ ላይ እንደሚገኙ የኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ፕሮጀክት ማኔጅመንት ኢንስቲትዩት ገልጿል።

የኢንስቲትዩቱት ጽህፈትቤት ኃላፊ አቶ ደምሰው መኮንን ለኢዜአ እንደገለጹት ስልጠናው የዘርፉ ተዋንያን ፕሮጀክት በተቀመጠለት ጊዜና ገንዘብ በጥራት ሰርተው በማስረከብ በኩል ያለባቸው ማነቆ እንዲፈቱ የሚያግዝ ነው።

በእምስት ቀናት የሚሰጠውስልጠና የፕሮጀክት ዲዛይንና ጥራት፣የፕሮጀክት ቅንጅትና አፈፃፀም፣ የፕሮጀክት ግንባታና ለኅብረተሰቡ የሚሰጡት ፋይዳ የሚሉት ርዕሰ ጉዳዮች ተካተውበታል።

ከስልጠናው ተሳታፊዎች የትግራይ ክልል በህንፃ ግንባታ የተሰማሩት ኢንጂነር መላኩ ተስፋይ ስልጠናው በኮንስትራክሽን ኢንደስትሪ ዘርፍ የተሰማሩ ባለሃብቶች በተፈለገው መንገድ ሰርተው የተጠበቀውን ፕሮጀክት በማስረከብ ኃላፊነታቸው እንዲወጡ እንደሚያደርግ እምነታቸውን ገልጸዋል።

በኮንስትራሽን ስራ የተሰማሩ አቶ ታምሩ በየነ በበኩላቸው ስልጠናው በመንግስትና በግል ዘርፉ ያሉት የዘርፉ ባለሙያዎች ከፕሮጀክት ዲዛይን እስከ ግንባታ ፍጻሜ ድረስ ተመካክረው ለመሥራት እንደሚያስችላቸው ተናግረዋል።

''የምንሰራው ግንባታ ለግል ጥቅማችን እንድናስብ ብቻ ሳይሆን፣ ለህዝባችንና አገራችን የሚኖረው ፋይዳ ግምት ውስጥ እንድናስገባ ያነሳሳል'' ሲሉም ተናግረዋል።

ኢንስቲትዩቱ ባለፉት አራት ዓመታት በፊት ከ10ሺህ ለሚበልጡ የሥራ ተቋራጮች፣አማካሪዎችና  የምህንድስና ባለሙያዎች  ስልጠና እንደሰጠም አስታውሷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም