የመገናኛ ብዙሃን ነጻነት ዘላቂነት እንዲኖር መስራት እንደሚገባ ተጠቆመ

112

አዲስ አበባ ሚያዝያ 29/2011 የኢትዮጵያ ጋዜጠኞች ማህበር አሁን በአገሪቷ የተፈጠረው የመገናኛ ብዙሃን ነጻነት ዘላቂነት እንዲኖር መስራት ይገባል አለ፡፡

ማህበሩ የተመሰረተበትን 50ኛ ዓመት የወርቅ ኢዮ በልዩ ማጠቃላያ በዓል በተለያዩ ዝግጅቶች አክብሯል።  

የማህበሩ ፕሬዝዳንት አቶ መሰረት አታላይ በዚሁ ወቅት እንዳሉት፤ ማህበሩ ሙያው በኢትዮጵያ እያደገ እንዲመጣ የራሱን አበርክቶ አድርጓል።  

ሙያው እንዲያድግ ለማስቻል ከውጭ ባለሙያዎች በማስመጣት በዘርፉ የአገር ውስጥ ባለሙያዎች ስልጠናዎች እንዲወስዱ መደረጉን ጠቅሰዋል።

ጋዜጠኝነትና የሕዝብ ግንኙነት ባለሙያዎችን ወደ ውጭ በመላክ እንዲሰለጥኑ መደረጉን የገለጹት  ፕሬዝዳንቱ ሙያውን የሚያጎለብቱ የተለያዩ የውይይት መድረኮች መካሄዳቸውን ለአብነት ተናግረዋል።

ለዋና ዋና የመገናኛ ብዙሃን የሙያ መሳሪያዎችና ቁሳቁስ በማህበሩ በኩል ድጋፍ መደረጉ ጋዜጠኝነት በኢትዮጵያ እንዲጠናከር ማህበሩ ያለውን ቁርጠኝነት አመላካች ነው ሲሉም ተደምጠዋል።  

እንዲያም ሆኖ ማህበሩ በኢትዮጵያ የፕሬስ ነጻነት እንዲከበር በመታገል ረገድ የሚጠበቅበትን ያህል ርቀት እንዳልተጓዘ አንስተዋል።  

''የጋዜጠኞች መብት እንዲከበር ማድረግ ላይ ትርጉም ያለው ሥራ አልሰራንም፤ ማህበሩ የነበሩ ፖለቲካዊ ተጽዕኖዎችን በገለልተኝነት መንፈስ አለመጋፈጡ ሁሌም በቁጭት የምናነሳው ነው'' ነው ብለዋል። 

በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ የታሰረ ጋዜጠኛ አለመኖሩ የሚያስደስት መሆኑን ጠቅሰው መንግሥት የፕሬስ ነጻነት እንዲረጋገጥ የጀመራቸውን ጥረቶች አድንቀዋል።  

በመንግሥት በኩል አበረታች ነገሮች ቢታዩም በአገሪቷ ያሉ መገናኛ ብዙሃን ያለባቸውን ችግር ለይቶ በዘላቂነት እንዲፈቱ ማህበሩ መስራት ይጠበቅበታል ብለዋል።

የኢትዮጵያ መምህራን ማህበር ምክትል ፕሬዝዳንት አቶ ሽመልስ አበበ በበኩላቸው ማህበሩ የገጠመውን ውጣ ውረድ አልፎ ለዛሬ መብቃቱ ትልቅ ነገር ቢሆንም ወደ ፊት ግን ብዙ መስራት ይጠበቅበታል ብለዋል።  

''አሁን አገር በህመም ላይ ነች' ያሉት ምክትል ፕሬዝዳንቱ ጋዜጠኞች አገሪቷ ከህመሟ እንድትፈወስ ሙያዊ ኃላፊነታቸውን መወጣት አለባቸው" ሲሉም ነው ያመለከቱት።

ለኢትዮጵያ ከምንግዜም በላይ የጋዜጠኝት ሙያ የሚያስፈልግበት ጊዜ መሆኑን የገለጹት ደግሞ የፕሬስ ምክር ቤት ሊቀመንበር አቶ አማረ አረጋዊ ነው።

ጋዜጠኞች መጠናከር አለባቸው የሚሉት ሊቀ-መንበሩ በሙያው ውስጥ ያለን ሰዎች ተደራጅተን ለአገር መስራት አለብን የሚል መልዕክት አጋርተዋል።

አገር የሚገነባው መረጃ ያለው ማህበረሰብ ሲፈጠር እንደሆነ የተናገሩት አቶ አማረ ለሕዝቡ በቂ መረጃ ማቅረብ ላይ ሚዲያው ትልቅ ሀላፊነት አለበት ብለዋል።  

ማህበሩም የሚጠበቀበትን መስራት ላይ ከፍተኛ ጉድለት አሳይቷል፤ በቀጣይ ግን ጠንክሮ መስራት እንደሚኖርበት አስገንዝበዋል።

በበዓሉ አከባበር ላይ የማህበሩ መስራቾችና አጋር አካላት የእውቅና ሽልማት ስነ-ስርዓት ተካሂዷል።

ማህበሩ በ1961 ዓ.ም የጋዜጠኞች ክበብ በሚል ሲቋቋም ለምስረታው ሀሳብ ያፈለቁት ደግሞ አቶ አሳምነው ገብረወልድ፣ ማዕረጉ በዛብህና ከፋለ ማሞ ነበሩ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም