በኤክሳይዝ፣ ተርን ኦቨርና ተጨማሪ እሴት ታክስ ላይ ማሻሻያ ሊደረግ ነው

309

አዲስ አበባ ሚያዚያ 29/2011 በሚቀጥለው በጀት ዓመት በኤክሳይዝ፣ ተርን ኦቨርና ተጨማሪ እሴት ታክስ ላይ ማሻሻያ ሊደረግ መሆኑን የገንዘብ ሚኒስቴር አስታወቀ።

በአገሪቷ ባሉ ሁሉም የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ወጥ የሆነ የክፍያ ተመን ስርዓት መዘርጋቱም ይፋ ሆኗል።

በ2012 በጀት ዓመት ኤክሳይዝ፣ተርን ኦቨርና ተጨማሪ እሴት ታክስ ላይ ማሻሻያ በማድረግ ከ20 እስከ 30 ቢሊዮን ብር ተጨማሪ ገቢ ለመሰብሰብ መታቀዱን ገንዘብ ሚኒስቴር አስታውቋል።

የገንዘብ ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር እዮብ መኮንን በአንድ ዓመት ውስጥ በአገሪቷ በተካሄዱ የኢኮኖሚ ማሻሻያዎች ላይ ለአገር ውሰጥ መገናኛ ብዙሃን ማብራሪያ ሰጥተዋል።

የአገሪቷን የኢንቨስትመንት ማበረታቻ ወጥና ዓለም የደረሰበትን ደረጃ ታሳቢ ያደረገ እንዲሁም በኢንዱስትሪው ዘርፍየሚያጋጥሙ እጸጾችን ለመፍታት የታክስ ማሻሻያ ማድረግ አስፈላጊ መሆኑን ገልጸዋል።

ላለፉት ዓመታት ከፍተኛ የኢኮኖሚ ዕድገት ቢመዘገብም ከሁለትና ሶስት ዓመታት በፊት ባጋጠመው የማክሮ ኢኮኖሚ ሚዛን መዛባት ዕድገቱን ለማስቀጠል ፈታኝ እንደነበር ዶክተር እዮብ ገልጸዋል።

ለዚህም የገቢና ወጪ ንግድ አለመመጣጠን፣ከፍተኛ የመንግስት ኢንቨስትመንትና የዕዳ ጫና በምክንያትነት ጠቅሰዋል።

ባለፈው አንድ ዓመት ይህን ለማስተካከል ኢኮኖሚው ሊያመነጨው የሚችለውን ገቢ ለመሰብሰብ የገቢ አሰባሳቢ ግብረ ሃይል መቋቋሙንና አገር አቀፍ የገቢ ንቅናቄ መደረጉን ጠቅሰዋል።

በቀጣይም የታክስ መሰረቱን ለማስፋት አዲስ የኤክሳይዝ፣ ተጨማሪ እሴት ታክስ፣ የቁርጥ ግብር፣ የተርን ኦቨር ታክስ ማሻሻያ ይደረጋል ነው ያሉት።

ኢኮኖሚው ሊያመነጭ የሚገባውን ገቢ በአግባቡ በመሰብሰብ በትምህርት፣ ጤናና ግብርና ዘርፍ የሚያስፈልጉ መሰረተ ልማቶችን ለማሟላትም አቅም ይፈጥራል ብለዋል።

በሚቀጥለው በጀት ዓመት ኤክሳይዝ፣ተርን ኦቨርና ተጨማሪ እሴት ታክስ ላይ ማሻሻያ በማድረግ ከ20 እስከ 30 ቢሊዮን ብር ተጨማሪ ገቢ ለመሰብሰብ በየደረጃው ካሉ አካላት ጋር ውይይት እየተካሄደ መሆኑንም ዶክተር እዮብ ተናግረዋል።

የአገሪቷ የልማት ፍላጎት ብዙ ቢሆንም ገቢው ግን ውስን በመሆኑ ባለፈው አንድ ዓመት ከልማት አጋሮች በተለይም ከቻይና እና ከአውሮፓ ህብረት ጋር ጠንካራ ግንኙነት ተፈጥሯል።

ባለፉት ዘጠኝ ወራት 3 ነጥብ4 ቢሊዮን ብር ከልማት አጋሮች ለማግኘት ታቅዶ 4 ነጥብ 2 ቢሊዮን ብር መገኘቱንና 2 ነጥብ 86 ቢሊዮን ብሩ ወደ መንግስት ግምጃ ቤት መግባቱን አብራርተዋል።

የብድር አከፋፈሉ ላይ መሻሻሎች መኖራቸውንና በዘጠኝ ወሩ 14 ነጥብ ሁለት ቢሊዮን ብር ለመክፈል ታቅዶ 8 ነጥብ 6 ቢሊዮን ብር የውጭ ብድር መከፈሉን ገልጸዋል።

አብዛኞቹ የመንግስት ተቋማት የፋይናንስ ስርዓቱን ባልጠበቀ መልኩ ወጪ ያደርጉ እንደነበር ያስታወሱት ዶክተር እዮብ በተለይ በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ላይ ቸግሩ የከፋ ነው ብለዋል።

ችግሩን ለመፍታትም የፋይናንስ ስርዓቱ ላይ ማሻሻያ መደረጉንና በሁሉም ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ወጥ የሆነ የክፍያ ሰርዓት መዘርጋቱን አስረድተዋል።

ኤክሳይዝ ታክስ የቅንጦት እቃዎች ሆነው ዋጋቸው ጨመረም አልጨመረም መሰረታዊ በመሆናቸው ምክንያት የገበያ ፍላጎታቸው በማይቀንስ ዕቃዎች ላይ፣ እንዲሁም የሕብረተሰቡን ጤንነት የሚጎዱና ማህበራዊ ችግር የሚያስከትሉ ዕቃዎችን አጠቃቀም ለመቀነስ ሲባል የተጣለ ታክስ ነው፡፡

ታክሱ በሀገር ውስጥ በሚመረቱና ወደ አገር ውስጥ በሚገቡ በአንዳንድ የተመረጡ ዕቃዎች ላይ ብቻ የተጣለ ነው፡፡

ተጨማሪ እሴት ታክስ በፍጆታ እቃ ወይም በተጠቃሚ ወጪ ላይ የተመሰረተ ታክስ ሲሆን የሚሰበሰበውም ምርት ከውጭ ወደ አገር ውስጥ ሲገባ ወይም ማንኛውም ታክሱ የሚከፈልበት ዕቃና አገልግሎት ግብይት ሲካሄድበት፤ በታክስ ሰብሳቢው መሥሪያ ቤት የሚሰበሰብ የታክስ አይነት ነው፡፡

ተርን ኦቨር ታክስ ደግሞ በአገር ውስጥ በሚከናወን የዕቃ ወይም በአገልግሎት ሽያጭ ወቅት የሚጣል የታክስ አይነት መሆኑ ይታወቃል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም