የዴሞክራሲ ተቋማት ሙስናን በመታገል የመልካም አስተዳደር የማስፈን ሚናቸውን እንዲወጡ ተጠየቀ

67

አዲስ አበባ ሚያዝያ 29/2011 በኢትዮጵያ የሚገኙ የዴሞክራሲ ተቋማት በአገሪቱ ሙስናን  ለመታገልና መልካም አስተዳደርን ለማስፈን በሚደረገው ጥረት የበኩላቸውን ሚና እንዲወጡ የፌደራል ስነ-ምግባርና ፀረ-ሙስና ኮሚሽን አሳሰበ።

ኮሚሽኑ ቪዥን ኢትዮጵያ ኮንግረስ ፎር ዴሞክራሲ ከተሰኘ አገር በቀል መንግስታዊ ያልሆነ ድርጅት ጋር በመተባበር ያዘጋጀውና የዴሞክራሲ ተቋማት በፀረ-ሙስና ትግል እና መልካም አስተዳደር የማስፈን ተግባራት ሊኖራቸው የሚገባውን ሚና ማጎልበት ላይ ያለመ መድረክ ዛሬ አዲስ አበባ ውስጥ ተካሂዷል።

የፌደራል ስነ-ምግባርና ፀረ-ሙስና ኮሚሽን ኮሚሽነር አቶ አየልኝ ሙሉአለም በዚሁ ወቅት ሙስና ቴክኖሎጅና የስልጣኔ ደረጃ ሳይገድበው በየትኛውም ማህበረሰብ ስለሚፈፀም በትግሉ ውስጥ የዴሞክራሲ ተቋማት ተሳትፎ አስፈላጊ ነው ብለዋል።

እንደ አቶ አየልኝ ገለፃ የዚህ ዓይነቱ መድረክ ተቋማቱ በህዝቡ ዘንድ የዴሞክራሲ ባህል እንዲዳብር፣ የዜጎች ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብት እንዲከበር በማድረግ ሙስናን እንዲዋጉ የሚያግዝ መሆኑንም ተናግረዋል።

“ኢትዮጵያን ለማዳን ሙሰኞችን መሸከም ይብቃን” ያሉት የቪዠን ኢትዮጵያ ኮንግረስ ፎር ዴሞክራሲ ዋና ዳይሬክተር አቶ ታደለ ደርሰህ የሲቪክ ማህበራት በፀረ ሙስና ትግሉ ላይ ሚናቸውን እንዳይወጡ የተለያየየ ማነቆ ተፈጥሮባቸው እንደቆየ ገልፀዋል።

በአሁኑ ወቅት በዚህ ረገድ የመጣውን መሻሻል እንደመልካም አጋጣሚ በመጠቀም ማህበራቱ በአገሪቱ የዴሞክራሲ ባህልን በማዳበርና መልካም አስተዳደርን በማጠናከር በፀረ-ሙስና ትግሉ ተሳትፎ ማድረግ እንደሚገባቸውም አሳስበዋል።

በሠላም ሚኒስቴር የስነ ምግባር መከታተያ ክፍል ኃላፊ የሆኑት አቶ ወርቁ ሰንደቅ  ሙስና ፍትሃዊ ያልሆነ የኑሮ ልዩነት በመፍጠር ሰላምን ያደፈርሳል፤ በመሆኑም "ሙስናን መዋጋት የምርጫ ጉዳይ ሳይሆን ሀገራዊ ህልውና ነው" ብለዋል።

ሙስናን ለመዋጋት ይቻል ዘንድ ነፃ የሚዲያና ጠንካራ የዴሞክራሲ ተቋማት እንደሚያስፈልጉ በመድረኩ ላይ የቀረበው ሰነድ አመልክቷል።   

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም