የጅማ ዩኒቨርሲቲ ማህበረሰብ አባላት ግንቦት ሃያንና የአካባቢ ቀንን በጽዳት ዘመቻ አከበሩ

76
ጅማ ግንቦት 28/2010 የጅማ ዩኒቨርሲቲ ማህበረሰብ አባላት 27ኛ ዓመት የግንቦት 20 የድል በዓልና ዓለም አቀፍ የአካባቢ ቀንን በጽዳት ዘመቻ አከበሩ። በጽዳት ዘመቻ ሥራው ላይ የተሳተፉ የዩኒቨርሲቲው ሠራተኞችና ተማሪዎች ለሀገራዊ ፍቅርና አንድነት የበኩላቸውን እንደሚወጡ ተናግረዋል። የዩኒቨርሲቲው ማህበረሰብ አባላት የጽዳት ዘመቻውን ያከናወኑት በጅማ ከተማ በሚገኙ አራት የዩኒቨርሲቲው ኮሌጆች ሲሆን በእዚህም በግቢ ውስጥና ከጊቢ ውጭ ያሉ አካባቢዎችን አጽድተዋል፡፡ 27ኛውን የግንቦት 20 የድል በዓልና ዓለምአቀፍ የአካባቢ ጥበቃ ቀንን "ከፕላስቲክ የጸዳ አካባቢ እንፍጠር" በሚል መሪ ቃል ነው  በጽዳት ዘመቻ ያከበሩት ፡፡ በጅማ ዩኒቨርሲቲ ግብርናና እንስሳት ኮሌጅ የአስተዳደር ሠራተኛ የሆኑት አቶ ስለሺ ዳምጠው " የግንቦት ሃያን የድል በዓል ከዓለም አቀፍ የአካባቢ ቀን ጋር አጣምረን በአካባቢ ጽዳት ዘመቻ በማክበራችን ተደስቻለሁ " ብለዋል፡፡ ከጽዳት ዘመቻው ባለፈ በኮሌጁ የሚማሩ የኢትዮጵያ ልጆች ተዋደውና ተከባበረው እንዲቆዩ በቀጣይ የድርሻቸውን ለመወጣት ዝግጁ መሆናቸውን አመልክተዋል። በግማሽ ቀን የጽዳት ዘመቻ የተሳከ ሥራ መስራታቸውን የገለጹት አቶ ስለሺ በአንድነትና በመተባበር መስራታቸው  ስኬታማ አንዳደረጋቸው አስታውቀዋል፡፡ በዩኒቨርሲቲው ዋና ግቢ በተካሄደ የጽዳት ዘመቻ ላይ የተሳተፈችው የቢሮ አስተዳደር ባለሙያ ወይዘሮ እናትነሽ ወርቁ በበኩሏ በጽዳት ሥራው ላይ መሳተፏ ከሥራ አመራሮችና ሠራተኞች ጋር ለመቀራረብ እንዳገዛት ተናግራለች፡፡ በጽዳት ሥራው ከከፍተኛ አመራር ጀምሮ ሁሉም የዩኒቨርሲቲው ማህበረሰብ በእኩልነትና በአንድነት መሳተፉ ውጤታማ ሥራ ለመስራት ማስቻሉንና ይህም በሌሎች ሥራዎች ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት ጠቁማለች፡፡ "ሠራተኞች በአራት ቡድን ተከፍለን የግንቦት 20 የድል በአልና ዓለም አቀፍ የአካባቢ ቀንን በጽዳት ዘመቻ አክብረናል" ያሉት ደግሞ በጅማ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት የፋሲሊቲና የጠቅላላ አገልግሎት ቡድን መሪ አቶ ያለው ታመነ ናቸው። ባከናወኑት የጽዳት ሥራም ከኢኒስቲትዩቱ መግቢያ በር ጅምሮ እስከ ግብርና ኮሌጅ ድረስ የሚገኘውን ዋና መንገድ ንጹህና ለዓይን ማራኪ ማድረጋቸውን ተናግረዋል፡፡ የጅማ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ፕሮፌሰር ፍቅሬ ለሜሳ በበኩላቸው ከዚህን በፊት የግንቦት 20 የድል በዓልን በፓናል ውይይት፣ በስፖርታዊ ውድድና በሌሎች ዝግጅቶች በዩኒቨርሲቲው ሲከበር መቆየቱን አስታውሰዋል። ዘንድሮ በዓሉ የጽዳት ሥራ በማከናወን መከበሩን ገልጸው፣ ለእዚህም የዓለም የአካባቢ ቀን በእዚህ ሳምንት የሚከበር መሆኑና የጅማ ከተማ  የኦሮሚያ የከተማች ሳምንትን በቅርቡ የምታከብር መሆኗን በምክንያትነት ጠቅሰዋል። የግንቦት 20 ድል የብሔር፣ የጾታ፣ የሃይማኖት እኩልነት የተረጋገጠበት መሆኑን ገልጸው፣ "የዩኒቨርሲቲው ተማሪዎች በልዩነቶቻቸው ላይ ሳይሆን በአንድነትና በጋራ ጉዳዮቻቸው ላይ እንዲያተኩሩና መልካም ስብዕና የተላበሱ እንዲሆኑ እንሰራለን" ብለዋል። ለእዚህም የዩኒቨርሲቲው ማህበረሰብ አባላት የድርሻቸውን እንዲወጡ ጥሪ አቅርበዋል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም