ፊንላንድ ለኢትዮጵያ ከፍተኛ ትምህርት የምትሰጠውን ድጋፍ አጠናክራ እንድትቀጥል ተጠየቀ

1568

አዲስ አበባ ግንቦት 28/2010 ፊንላንድ ለኢትዮጵያ ከፍተኛ ትምህርት የምትሰጠውን ድጋፍ አጠናክራ እንድትቀጥል የኢፌዴሪ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዶክተር ወርቅነህ ገበየሁ ጠየቁ።

ሚኒስትሩ በፊንላንድ እያደረጉ ያሉትን ጉብኝት ቀጥለው በዛሬው ዕለት ከአገሪቷ ፕሬዝዳንት ሳውሊ ኒኒስቶ ጋር በሁለትዮሽና በአካባቢያዊ ጉዳዮች ላይ ተወያይተዋል።

ዶክተር ወርቅነህ በዚሁ ጊዜ ኢትዮጵያውያን በኢንጅነሪንግ እና አርክቴክቸር ዘርፎች በፊንላንድ መማራቸውን ጠቁመው፤ ይኸው የትምህርት ድጋፍ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ጠይቀዋል፡፡

“ኢትዮጵያ ከራሷ ሰላም አልፋ ለአፍሪካ ቀንድ ሰላም እየሰራች ነው” ያሉት ሚኒስትሩ፤ የሶማሊያን መንግስት የጸጥታ መዋቅር ለማሻሻል እንዲሁም የደቡብ ሱዳንን የሰላም ሂደት ለመደገፍ በሚደረገው ጥረት እገዛ እንዲያደርጉ ለፕሬዝዳንቱ ጥሪ አቅርበውላቸዋል ፡፡

ዶክተር ወርቅነህ አያይዘውም የክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይን የጉብኝት ግብዣ ለፕሬዝዳንት ሳውሊ ኒኒስቶ አቅርበውላቸዋል፡፡

ፕሬዝዳንቱም “ጉብኝቱ የሁለቱን አገሮች ግንኙነት እንደሚያጠናክር አምናለሁ” በማለት የጉብኝቱን ግብዣ መቀበላቸውን ገልጸዋል፡፡

“በየትኛውም ወቅት ከኢትዮጵያ ጋር እንቆማለን፤ በአገሪቷ የተካሄደውን የፖለቲካ ማሻሻያም እንደግፋለን” ያሉት ፕሬዝዳንቱ፤ “በደቡብ ሱዳንና በሶማሊያ ሰላም ጉዳይ ላይም ከኢትዮጵያ ጋር በጋራ እንሰራለን” ብለዋል፡፡

በተመሳሳይ ዶክተር ወርቅነህ ከፊንላንድ አቻቸው ቲሞ ሶይኒ እንዲሁም ከአገሪቷ ፓርላማ የውጭ ግንኙነት ቋሚ ኮሚቴ አባላት ጋር ውይይት አድርገዋል፡፡

በዚህም ወቅት በኢትዮጵያ እየተካሄደ ያለውን የፓለቲካ ምህዳር ማስፋት በተመለከተ ሚኒስትሩ ገለጻ መስጠታቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ጽሕፈት ቤት ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት የላከው መረጃ ያሳያል፡፡

ፊንላንድ ከኢትዮጵያ ጋር ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነቷን የጀመረችው እ.አ.አ በ1959 ሲሆን፤  ኤምባሲዋን በአዲስ አበባ የከፈተችው ደግሞ በ1965 ነው። ይህ የፊንላንድ የአዲስ አበባ ኤምባሲም ከሰሐራ በታች ካሉት የአገሪቷ ኤምባሲ የመጀመሪያው መሆኑን መረጃዎች ይጠቁማሉ።