በሙስና ወንጀል የተጠረጠሩ ነጋዴዎች ክስ ተመሰረተባቸው

560

ሚያዝያ 29/2011 ከኢትዮጵያ ውኃ ሥራዎች ኮንስትራክሽን ድርጅት ጋር በተያያዘ በከባድ የሙስና ወንጀል የተጠረጠሩ ነጋዴዎች ክስ የተመሰረተባቸው መሆኑን የፌዴራል ጠቅላይ አቃቤ ህግ ገለጸ።

ክስ የተመሰረተባቸው ነጋዴዎች 1ኛ አቶ ክፍሌ አብርሃም፣ 2ኛ አቶ ደጉ ተካ፣ 3ኛ አቶ ዕቁባይ ዮሐንስ፣ 4ኛ አቶ ጥጋቡ ኃይለኢየሱስ እና 5ኛ አቶ ይስሐቅ ወልደ ጻድቅ ናቸው።

ተከሳሾቹ ከርብ ግድብና መስኖ ልማት ፕሮጀክት ጋር በተያያዘ ከባድ የሙስና ወንጀል  ፈጽመዋል ተብለው በመጠርጠራቸው ነው ክሱ የተመሰረተባቸው፡፡

የኢትዮጵያ ውኃ ሥራዎች ኮንስትራክሽን ድርጅት የርብ ግድብና መስኖ ልማት ፕሮጀክት  ሥራ አስኪያጅ ሆነው ሲሠሩ ከነበሩት ከአቶ ሽመልስ ገበረ ሥላሴና አቶ አሳየኸኝ ወልዴ ጋር በጥቅም በመመሳጠር በሙስና ወንጀል ሰርተዋል ተብለው በመጠርጠራቸው ነው።

ተከሳሾቹ የተለያዩ ኤክስካቫተር ማሽነሪዎችን ለኢትዮጵያ ውኃ ሥራዎች ኮንስትራክሽን  ድርጅት የርብ ግድብና መስኖ ልማት ፕሮጀክት ግንባታ ለማቅረብና አገልግሎት ለመስጠት ያልተገባ ውል ተዋውለዋልም ተብሏል።

የክስ መዝገቡ እንደሚያስረዳው ተሳሾቹ በልዩ ወንጀል አድራጊነት በፈጸሙት ከባድ  የሙስና ወንጀል ተጠርጥረዋል።

ዐቃቤ ሕግ በተከሳሾች ላይ የመሰረተው የክስ ጭብጥ በችሎቱ ለቀረቡ ተከሳሾች ተነቦ እንዲረዱት የተደረገ ሲሆን፤ በቀረበባቸው ክስ ላይ ያላቸውን አስተያየት እንዲሰጡ በተሰጠው እድል የዋስትና መብታቸው እንዲከበርላቸው ጠይቀዋል፡፡

ዐቃቤ ሕግ በበኩሉ ተፈጸመ የተባለው ወንጀል የዋስትና መብትን የሚያስከለክል በመሆኑ የዋስትና መብት ሊፈቀድላቸው አይገባም በማለት ተቃውሞውን ለፍርድ ቤቱ አቅርቧል፡፡

የግራ ቀኙን ክርክር የተመለከተው የፌደራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 15  ወንጀል ችሎት በፍርድ ቤቱ ያልቀረቡ ሌሎች ተከሳሾችን የፌደራል ፖሊስ በቀጣይ ቀጠሮ ይዞ እንዲያቀርብ ትዕዛዝ በመስጠት ለግንቦት 07 ቀን 2011 ዓ.ም ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡