በአቶ ጌታቸው አሰፋ ላይ ክስ ተመሰረተ

101

ሚያዝያ 29/2011 የቀድሞውን የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት ሃላፊ አቶ ጌታቸው አሰፋን ጨምሮ በ26 የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት የሥራ ኃላፊዎች ላይ ክስ ተመሰረተ።

አቶ ጌታቸው አሰፋን ጨምሮ በ26 የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት የሥራ ኃላፊዎችና  ሰራተኞች ላይ ክስ መመስረቱን የፌዴራል ጠቅላይ አቃቤ ህግ አስታወቀ።

ከባድ የሰብዓዊ መብት ጥሰት ፈጽመዋል በሚል በፌደራል ፖሊስ ወንጀል መርማሪዎች፤  በማረሚያ ቤት የሥራ ኃላፊዎች እንዲሁም በብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት የሥራ ኃላፊዎች ላይ የወንጀል ምርመራ ሲካሔድ መቆየቱ ይታወሳል፡፡

በዚሁ መሰረት ዐቃቤ ሕግ በወንጀል መርማሪዎች፣ በማረሚያ ቤቱ የሥራ ኃላፊዎች ላይ እንዲሁም በብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት የስራ ኃላፊዎችና ሰራተኞች ላይ በሶስት የተለያዩ መዝገቦች ክስ ተመስርቷል፡፡

በመርማሪዎች ላይ በፌደራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት የተከፈተው እና በማረሚያ ቤት ኃላፊዎች በነበሩት ላይ በፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት የተከፈቱት መዛግብት የክስ ሂደቱ ቀጥሎ ምስክር ለመስማት ተቀጥረዋል፡፡

በሶስተኛውና በዚህኛው የመጨረሻ መዝገብ ላይ 26 የብሔራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት የሥራ ኃላፊዎችና ሰራተኞች በጠቅላላው 46 ክሶች ተመስርቶባቸዋል።

በክሶቹ ውስጥ 22ቱ ተከሳሾች በአሁኑ ወቅት በእስር ላይ የሚገኙ ናቸው፤ በሌላ በኩል የቀድሞ የአገልግሎቱ ዋና ዳይሬክተር አቶ ጌታቸው አሰፋን ጨምሮ አቶ አጽብሃ ግደይ፣ አቶ አሠፋ በላይ እና አቶ ሽሻይ ልዑል በተባሉ የቀድሞ የሥራ ኃላፊዎች ላይ ዛሬ  ሚያዚያ 29 ቀን 2011 ዓ.ም በሌሉበት  በከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ ችሎት ክስ ይመሰረትባችዋል፡፡

በአቶ ጌታቸው ላይ በ1996 ዓ.ም የወጣውን የወንጀል ህግ አንቀጽ 32/1/ (ሀ) (ለ) እና 407/1/ (ለ) (ሐ) እና 407/3/ ላይ የተደነገገውን በመተላለፍ ስልጣንን ያለአግባብ መገልገል ከባድ የሙስና ወንጀል መፈጸም እንዲሁም በ1996 ዓ.ም የወጣውን የወንጀል ህግ አንቀጽ 32 (1) ሀ እና ለ እንዲሁም የሙስና ወንጀሎችን ለመደንገግ የወጣውን አዋጅ ቁጥር 881/2007 አንቀጽ 9 /1/ (ለ) እና (ሐ) እና 9/3/ ላይ የተደነገገውን በመተላለፍ ስልጣንን ያለአግባብ መገልገል ከባድ የሙስና ወንጀል ፈጽመዋል በሚል ክስ ቀርቦባቸዋል፡፡

በሌሎቹ ሁሉም ተከሳሾች ላይ በ1996 ዓ.ም የወጣውን የወንጀል ህግ አንቀጽ 32/1/ (ሀ) (ለ) እና 407/1/ (ለ) (ሐ) እና 407/2/ ላይ የተደነገገውን በመተላለፍ ስልጣንን ያለአግባብ መገልገል ከባድ የሙስና ወንጀል መፈጸም እንዲሁም በ1996 ዓ.ም የወጣውን የወንጀል ህግ አንቀጽ 32 (1) ሀ እና ለ እንዲሁም የሙስና ወንጀሎችን ለመደንገግ የወጣውን አዋጅ ቁጥር 881/2007 አንቀጽ 9 /1/ (ለ) እና (ሐ) እና 9/2/ ላይ የተደነገገውን በመተላለፍ ስልጣንን ያለአግባብ መገልገል ከባድ የሙስና ወንጀል ፈጽመዋል በሚል ክስ ተመስርቶባቸዋል፡፡

ሥልጣንን ያለአግባብ መገልገል ክስ ሊቀርብባቸው የቻለው ተከሳሾች በግልጽ ከተሰጣቸው ሥልጣን ወይም ኃላፊነት አሳልፈው በመስራት እንዲሁም ሥልጣናቸው ወይም ኃላፊነታቸው የማይፈቅድላቸውን በተለይም ሥልጣን ወይም ኃላፊነት ሳይኖራቸው በሌላ ሰው መብት ላይ ጉዳት እንዲደርስ በማሰብ በተበዳዮች ላይ ከባድ የሰብዓዊ መብት ጥሰት በመፈጸማቸው ነው፡፡

በአቶ ጌታቸው ላይ በንዑስ አንቀጽ 3 መሰረት ክስ ሊቀርብባቸው የቻለው 
1ኛ) በሚኒስትር ማዕረግ የተቋሙ ዋና ዳይሬክተር ጀነራል የነበሩ በመሆናቸው፣ የኃላፊነት ወይም የሥልጣን ደረጃቸው ከፍተኛ በመሆኑ፣ 
2ኛ) ኃላፊነታቸውን የጣሱበት ዓላማ ከባድ በመሆኑ እንዲሁም 
3ኛ) በሕዝቦች ወይም በተጎጂዎች ላይ የደረሰው ጉዳት ከባድ በመሆኑ የተፈጸመውን ወንጀል ከባድ ሊያደርገው በመቻሉ ነው፡፡

ቀሪዎቹ ተከሳሾች በሙሉ በንዑስ አንቀጽ 2 መሰረት ክስ ሊቀርብባቸው የቻለው ከላይ ለአቶ ጌታቸው ወንጀል ከባድነት ከተጠቀሱት ምክንያቶች ውስጥ ቢያንስ አንዱ ተሟልቶ በመገኘቱ ነው፡፡

አቶ ጌታቸውን ጨምሮ በአራቱ ተከሳሾች ላይ በሌሉበት ክስ ሊመሰረት የቻለው ደግሞ በወንጀለኛ መቅጫ ህግ ስነ-ስርዓት ቁጥር 42/1/ለ እና 161/2/ሀ መሰረት ተከሳሾች የቀረቡባቸው ክሶች ከባድ በመሆናቸው በህጉ መሰረት በሌሉበት ክስ ሊቀርብባቸው የሚገባ በመሆኑ ነው፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም