አገር አቀፍ ተደራዳሪ ፓርቲዎች በመጪው ሰኞ በብሄራዊ መግባባት ድርድራቸውን ለመጀመር ተስማሙ

42
አዲስ አበባ ግንቦት 28/2010 አገር አቀፍ ተደራዳሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች በ"ብሄራዊ መግባባት" ጉዳይ ላይ ድርድር መጀመር ይቻል ዘንድ ሊኖር በሚገባው የመወያያ ማዕቀፍ ላይ የሀሳብ ልዩነት በመፈጠሩ ድርድሩ ከዚህ በፊት ይመራበት በነበረው አቅጣጫ መሰረት እንዲቀጥል ተስማምተዋል። ፓርቲዎቹ ከኢትዮጵያ ህዝቦች አብዮያዊ ዴሞክራሲያዊ ግንባር (ኢህአዴግ) ጋር በነበረው መርሃ ግብር መሰረት ድርድሩን ለመቀጠል ለመጪው ሰኞ ቀጠሮ ይዘው ተለያይተዋል። ተደራዳሪ ፓርቲዎቹ ባለፈው ሳምንት ረቡዕ ባካሄዱት ስብሰባ በ"ብሄራዊ መግባባት" ርእሰ ጉዳይ ዙሪያ የሚካሄደው ድርድር ሊኖረው በሚገባው  አቅጣጫና ማዕቀፍ ላይ የተነጋገሩ ቢሆንም በስምምነት መቋጨት ባለመቻላቸው ለዛሬ ቀጠሮ ይዘው ነበር። በዛሬው እለት በተካሄደው ስብሰባ በርእሰ ጉዳዩ ዙሪያ ከየፓርቲዎቹ የቀረበው ሃሳብ የተበታተነና ያልተቀናጀ በመሆኑ ሀሳቦቹን በማቀናጀት የድርድር መርሃ ግብር የሚያዘጋጅ አካል ማቋቋም ያስፈልጋል፤ ይህ አካል በማንና እንዴት መቋቋም ይኖርበታል በሚለው ጉዳይ  ላይ ተወያይተዋል። በዚሁ ጊዜም አስሩ አገር አቀፍ ተደራዳሪ ፓርቲዎች የመደራደሪያ ሀሳቦቹን በማቀናጀት የድርድር ማዕቀፍ መርሃ ግብር የሚያዘጋጅ በባለሙያዎች የሚታገዝ ኮሚቴ እንዲቋቋም ሀሳብ አቅርበዋል። በሌላ በኩል ደግሞ ኢሶዴፓ፣ መኢብን፣ ገዳ ስርአት አራማጅና መኦህዴፓ 'የቀረቡት ሀሳቦች ተቀናጅተው መቅረብ ያለባቸው በኮሚቴ ሳይሆን በባለሙያ ነው፤ ይህ ካልሆነ ግን ከዚህ በፊት ሲሰራበት የነበረውን የድርድር ሂደት በመከተል ድርድሩን መቀጠል ይገባል' የሚል አቋም አንፀባርቀዋል። ኢህአዴግ በበኩሉ ሀሳቦቹን በባለሙያዎችም ሆነ በኮሚቴ አቀናጅቶና ማዕቀፍ አዘጋጅቶ ለሚቀርብ አካል ድጋፍ እንደሚያደርግ ገልጿል። ያም ሆኖ ተደራዳሪ ፓርቲዎቹ በዚህ መልኩ መስማማት ባለመቻላቸው ድርድሩ ከዚህ በፊት ሲመራበት በነበረው የድርድር ሂደት እንዲቀጥል በመወሰን ተለያይተዋል። በዚህም መሰረት ፓርቲዎቹ በአምስተኛ ደረጃ ላይ በተቀመጠው "የብሄራዊ መግባባት" ጉዳይ ድርድራቸውን ለመቀጠል ለቀጣይ ሳምንት ቀጠሮ ይዘዋል፡፡
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም