ከአውሮፕላን ነዳጅ በስተቀር የሁሉም ነዳጅ ምርቶች የችርቻሮ ዋጋ በሰኔ ወርም ባለበት ይቀጥላል

112
አዲስ አበባ  ግንቦት 28/2010 በግንቦት ወር ተግባራዊ እየተደረገ ያለው የነዳጅ ምርቶች የችርቻሮ ዋጋ ከግንቦት 29 ጀምሮ እስከ  ሰኔ 30 ድረስ  ባለበት እንደሚቀጥል የንግድ ሚኒስቴር አስታወቀ። የሚኒስትሮች ምክር ቤት በመስከረም 2001 ባደረገው  መደበኛ ስብሰባው የነዳጅ ምርቶች የችርቻሮ ዋጋ በየወሩ እንዲከለስ መመሪያ ማስቀመጡ ይታወሳል። ንግድ ሚኒስቴር ለኢዜአ በላከው መግለጫ እንዳስታወቀው፤ ከአውሮፕላን ነዳጅ ዋጋ በስተቀር የሌሎች ነዳጅ ምርቶች ዋጋ ባለበት የሚቀጥል ይሆናል። 'በግንቦት ወር የነበረው የነዳጅ ምርቶች  የዓለም ዋጋ ከባለፈው  ወር ጋር ሲነጻጸር በሁሉም የነዳጅ ምርቶች ላይ ጭማሪ አሳይቷል' ያለው ሚኒስቴሩ፤ የአገሪቱ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ በተረጋጋ ሁኔታ እንዲቀጥል ለማስቻል ጭማሪ አለመደረጉን አመልክቷል። የአውሮፕላን ነዳጅ ዋጋ በግንቦት ወር ይሸጥበት ከነበረው 23 ከ 80 ብር በዓለም ወቅታዊ ዋጋ አማካይነት ተሰልቶ በተገኘው ልዩነት 2 ብር ከ11 ሳንቲም  በመጨመር በሊትር ብር 25 ከ91 ሳንቲም እንዲሆን ተደርጓል። በዓለም ገበያ የሚኖረውን የነዳጅ ዋጋ መነሻ በማድረግ እንደ አስፈላጊነቱ የዋጋ ማስተካከያዎች ሊደረጉ እንደሚችሉ ሚኒስቴሩ በላከው መግለጫ  አመላክቷል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም