ለዓይን ሞራ ግርዶሽ ተጠቂዎች ወቅቱን የጠበቀ ህክምና መስጠት አልተቻለም-የአማራ ክልል ጤና ቢሮ

63

ሚያዝያ 28/2011 ለዓይን ሞራ ግርዶሽ ተጠቂዎች ወቅቱን የጠበቀ ህክምና መስጠት እንዳልቻለ የአማራ ክልል ጤና ቢሮ አስታወቀ፡፡

ባለፉት ዘጠኝ ወራት ህክምናውን ያገኙ ሰዎች ቁጥር ከ3ሺህ አይበልጥም።

በቢሮው ትኩረት የሚሹ በሽታዎች ባለሙያ አቶ መልካሙ በየነ ለኢዜአ እንደገለጹት በክልሉ ከ1 ሚሊዮን በላይ ሰዎች በበሽታው ምክንያት ለዝቅተኛ የዕይታ ችግር ተጋልጠዋል።

"በዘርፉ የባለሙያዎች እጥረትና ህክምናውን የሚሰጥባቸው ጤና ተቋማት ውስን መሆን ለተጠቂዎች ወቅቱን የጠበቀ ህክምና እንዳይሰጥ አድርጓል" ብለዋል።

በክልሉ ከሚገኙ ከ67 በላይ ሆስፒታሎች ውስጥ የዓይን ቆብ ቀዶ ህክምና የሚሰጡት ሰባት ብቻ መሆናቸውን ለአብነት ጠቅሰዋል።

በዘርፉ የሰለጠኑ ባለሙያዎች ቁጥር አነስተኛ በመሆናቸው ህክምናውን ተደራሽ ማድረግ አንዳልተቻለም ገልጸዋል።

አንድ ሆስፒታል በዓመት ለ2ሺህ ሰዎች ህክምና እንዲያደርግ ቢታቀድም፤ ባለፉት ዘጠኝ ወራት በሆስፒታሎቹ በመደበኛና በዘመቻ ህክምናው የተሰጣቸው ሰዎች ከ3ሺህ እንደማይበልጡ ተናግረዋል።

የዓይን ሞራ ግርዶሽ በእድሜ መግፋት የሚከሰትና በወቅቱ ታክሞ ከመዳን ውጭ የማይከላከሉት መሆኑን የገለጹት ባለሙያው፣ "በክልሉ በወቅቱ ህክምና ማግኘት ያልቻሉ 300ሺህ ሰዎች ሙሉ በሙሉ የዓይን ብርሃናቸውን እንዳጡ ከሶስት ዓመት በፊት በተካሄደ ጥናት ተረጋግጧል" ብለዋል።

እንደ ባለሙያው ገለጻ እስከ 2014 ድረስ በሁሉም ሆስፒታሎች የቀዶ ጥገና ህክምናውን በመስጠትና የባለሙያዎች ቁጥር በማሳደግ ህክምናውን ተደራሽ ለማድረግ ከባለድርሻ አካላት ጋር በትብብር እየተሰራ ነው።

የባህርዳር ፈለገ-ሕይወት ሪፈራል ሆስፒታል ከአሜሪካው “ሄልሚን የዓይን ሞራ ግርዶሽ ፕሮጀክት “ ጋር በመተባበር ሰሞኑን ለ400 ሰዎች የዓይን ሞራ ግርዶሽ ቀዶ ህክምና ሰጥቷል።

የሄልሚን የዐይን ሞራ ግርዶሽ ፕሮጀክት” ሜዲካል ዳይሬክተር ዶክተር ማት ኦሊቫ በዓይን ሞራ ግርዶሽ ምክንያት የሚከሰት ዓይነ-ስውርነት ከእድሜ መግፋት ጋር ተያይዞ እንደሚከሰት ገልጸዋል።

የዐይን ሞራ  ግርዶሽ ለዓይነ ስውርነት ከሚዳርጉ በሽታዎች መካከል በዋነኝነት የሚጠቀስ ቢሆንም፤ በቀላሉ የቀዶ ጥገና ህክምና በማድረግ የዓይን ብርሃንን ወደ ነበረበት መመለስ እንደሚቻል ገልጸዋል።

በፈለገ  ህይወት ሪፈራል ሆስፒታል በቁ የዓይን ህክምና  ባለሙያዎች ስላሉ ህክምናውን ለማገኘት ወደ ባህርዳር የሚመጡ ሰዎች በርካታ መሆናቸውን የገለጹት ሜዲካል ዳይሬክተሩ፣"ባለሙያዎችን በማብዛት ኅብረተሰቡን ከጉዳት መታደግ ይገባል" ብለዋል።

የፈለገ-ሕይወት ጠቅላላ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል የዓይን ህክምና ስፔሻሊስት ዶክተር ህይወት ደግነህ በበኩላቸው በክልሉ የዓይን ህክምና ተቋማት ውስንነት ቢኖርም፤ኅብረተሰቡ አገልግሎቱን ወደሚሰጡ ተቋማት በመሄድ ራሱን ከጉዳት ሊታደግ እንደሚገባ መክረዋል ።

"ኅብረተሰቡ የዓይኑ የማየት አቅም እየቀነሰ ሲመጣ፣ በተለይ ቀለሞችን ከርቀት የመለየት ችግር ሲገጥመውና ጭጋግ ሲያለብሰው ቶሎ ወደ ህክምና ተቋማት መሄድ ይጠበቅበታል" ሲሉም መክረዋል።

አርሶ አደር ገነት ብርሃኑ የ25 ዓመት ወጣት ናቸው። ከአንድ ዓመት በፊት የሁለቱም ዓይኖቻቸው የማየት አቅም አጥቶ ከወራት ወዲህ ሙሉ በሙሉ ማለት ማቆማቸውን ተናግረዋል ።

በተደረገላቸው ህክምና ማየት በመቻላቸው መደሰታቸውን ገልጸው፣ 'ሌሎች ተጠቂዎች  ወደ ህክምናውን እንዲያደርጉ  ምክራቸውን ለግሰዋል።

ከሁለት ዓመታት በፊት የዓይናቸውን ብርሃን እንዳጡ የገለጹት እማሆይ ለምለም ዓለማየሁ በበኩላቸው በተደረገላቸው ህክምና ማየት ችያለሁ ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም