ሆስፒታሉ በህክምና መሳሪያዎችና በባለሙያዎች እጥረት ተገቢውን የህክምና አገልግሎት ለመስጠት አንዳልቻለ ገለጸ

55

ምቤላ ሚያዝያ 28 ቀን 2011 በጋምቤላ ክልል የኝንኛንግ የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል በህክምና መሣሪያዎችና በባለሙያዎች እጥረት ተገቢውን የህክምና አገልግሎት ለመስጠት አልቻልኩም አለ።

የክልሉ ጤና ጥበቃ ቢሮ ኝንኛንግን ጨምሮ በክልሉ በሚገኙ አራት ሆስፒታሎች ያለውን ችግሮቹን ለመፍታት እየተሰራ መሆኑን ገልጿል።

የሆስፒታሉ ሥራ አስኪያጅ አቶ ጋትቤል ጋርማል ለኢዜአ እንደገለጹት በሆስፒታሉ በቂ የህክምና መሣሪያዎችና ባለሙያዎች በመጓደላቸው አገልግሎቱን በተሟላ መልኩ እየተሰጠ አይደለም።

ለሆስፒታሉ ከአራት ዓመታት በፊት በከፍተኛ ወጪ የተገዙት የህክምና መሣሪያዎች ባለመተከላቸው ለብልሽት እየተዳረጉ መሆናቸውንም ተናግረዋል።

ለተከላው የክልሉ ጤና ጥበቃ ቢሮ ባለሙያዎች እንዲመደብላቸው ቢያሳዉቁም፣ እስካሁን ምላሽ አለማግኘታቸውንም  ገልጸዋል። 

በሆስፒታሉ ባሉት ችግሮች ምክንያት ወላዶችን ጨምሮ ታካሚዎችን ወደ ጋምቤላ ሆስፒታል ለመላክ መገደዳቸውን አቶ ጋትቤል አስታውቀዋል ።

ለሆስፒታሉ የውሃና የኤሌክትሪክ አገልግሎት አቅርቦት ችግሮች  አፋጣኝ ምላሽ እንዲሰጥበት ሥራ አስኪያጁ ጠይቀዋል።

የጋምቤላ ክልሉ ጤና ጥበቃ ቢሮ ኃላፊ አቶ ካን ጋልዋክ ሆስፒታሉ ያቀረበው ቅሬታ አግባብነት ያለው ነው ብለዋል።

ችግሩ ከአራት ዓመታት በፊት የኝንኛንግን ጨምሮ ለአራት ሆስፒታሎች ከጤና ሚኒስቴር የተላኩ የህክምና መሣሪያዎች ሳይተከሉ በመቆየታቸው እንደሆነም ያስረዳሉ።

ከሚኒስቴሩ ባለሙያዎችን በመጠየቅ በሆስፒታሎቹ ያለውን ችግር በቅርቡ ለመፍታት ጥረት እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል።

በሆስፒታሉ የባለሙያዎች እጥረት ያጋጠመው  የሚያስፈልገው በጀት ባለመያዙ ነው ያሉት ኦቶ ካን ፣ በሚቀጥለው በጀት ዓመት በጀት ለማስያዝ ጥረት እንደሚደረግ ተናግረዋል።

በኝንኛንግ፣ በፉኝዶና በኩሚ የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታሎች የኤሌክትሪና የውሃ አቅርቦት ችግሮችን ለመፍታት ቢሮው ከኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎትና ከክልሉ ውሃና  መስኖ ኤሌክትሪክ ልማት ቢሮ ጋር እየሰራ ነው ብለዋል።

የኝንኛንግ የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል ተገንብቶ አገልግሎት መስጠት ከጀመረ ሁለት ዓመታትን አስቆጥሯል።

የኝንኛንግ የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል በኑዌር ዞን አምስት ወረዳዎች ለሚገኝ 100ሺህ ሕዝብ አገልግሎት ይሰጣል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም