በደቡብ ክልል 399 ጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞች ወደ መካከለኛ ደረጃ ተሸጋገሩ

87
ሃዋሳ ግንቦት 28/2010 በደቡብ ክልል በአምራች ዘርፉ ተሰማርተው ራሳቸውን መለወጥ የቻሉ 399 ጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞች ዛሬ ዕውቅና ተሰጥቷቸው ወደ መካከለኛ ደረጃ ተሸጋገሩ፡፡ በተሰማሩበት መስክ ጠንክረው በመስራት ከራሳቸው ባለፈ ለሌሎች የስራ ዕድል መፍጠራቸውን ኢዜአ ያነጋገራቸው ኢንተርፕራይዞች ገልጸዋል፡፡ የደቡብ ክልል ንግድና ኢንደስትሪ ቢሮ ኃላፊ ዶክተር ጌትነት በጋሻው በዕውቅና ስነስርዓቱ ላይ እንዳሉት መንግስት ስራ አጦችን በተለያዩ መስኮች በማሰማራት ተጠቃሚ እንዲሆኑ እያደረገ ነው፡፡ በክልሉ ከ5 ሺህ 500 በላይ ኢንተርፕራይዞች በተለያዩ መስኮች የስራ እድል እንደተፈጠረላቸውም ገልፀዋል፡፡ በክልሉ ከሚገኙ 14 ዞኖችና አራት ልዩ ወረዳዎች ላለፉት አምስት ዓመታት በማህበር ተደራጅተው ወደ ስራ ከገቡት ከእነዚሁ ጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርኘራይዞች መካከል ሀብታቸውን ከ1 ሚሊዮን በላይ ማድረስ የቻሉት 399 ኢንተርኘራይዞች ዛሬ እውቅና ተሰጥቷቸው ወደ መካከለኛ ደረጃ ተሸጋግረዋል፡፡ የክልሉ መንግስት የኢንደስትሪ ልማቱን የሚያፋጥኑ ማህበራትን የዕድገት ደረጃ ግምት ውስጥ በማስገባት በገበያ ብቁና ተወዳዳሪ እንዲሆኑ ለማድረግ የአቅም ግንባታ ስራዎችን እየሰራ መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡ የብድር፣ የማምረቻና መሸጫ ቦታዎችን አዘጋጅቶ ከማቅረብ ባለፈ ከተለያዩ መንግስታዊና መንግስታዊ ካልሆኑ ተቋማት ጋር በመነጋገር የገበያ ትስስር መፈጠሩንም ዶክተር ጌትነት ተናግረዋል፡፡ የማሽነሪ አቅርቦት ችግር፣ መሰረተ ልማት የማሟላት፣ የማምረቻና የመሸጫ ቦታዎችን ለታለመላቸው አላማ ከማዋል አንጻር የሚስተዋሉ ውስንነቶችና የኪራይ ሰብሳቢነት አመለካከቶች በስራው ላይ ያጋጠሙ እንቅፋቶች መሆናቸውንም ገልጸዋል፡፡ በሲዳማ ዞን ዳራ ወረዳ በእንጨትና ብረታ ብረት ማምረት ስራ የተሰማራው አንድነት ማህበር ሰብሳቢ ወጣት ሞገስ ግርማ እንዳለው ስምንት ሆነው በ6 ሺህ ብር መነሻና የ20 ሺህ ብር ብድር የተጀመረው ስራ ዛሬ የሶስት ሚሊዮን ብር ሀብት ባለቤት አድርጓቸዋል፡፡ በማህበር ተደራጅተው ወደ ስራ ከገቡት ውስጥ ሶስቱ የራሳቸውን ማምረቻ ከፍተው መልቀቃቸውንና ለአምስት ሰዎች የስራ እድል መፍጠር እንደቻሉ ተናግሯል፡፡ በጌዴኦ ዞን ዲላ ከተማ ሻላዬ የባህል አልባሳት ስራ ማህበር ሰብሳቢ ወይዘሪት ፈለቀች ጌታቸው እንዳለችው አራት ማህበራት አንድ ላይ በመሆን በ2006 ዓ.ም ወደ ስራ መግባታቸውን ተናግራለች፡፡ የተለያዩ የባህል አልባሳትን በማምረት ለሀገር ውሰጥ ገበያ በማቅረብ ከ300 ሺህ ብር በላይ ጥሬ ገንዘብ እንዳላቸውና ከባህል አልባሳት በተጨማሪ የጌዴኦን ቡና በማስተዋወቅ ጭምር እየሰሩ እንደሚገኙ ገልጻለች፡፡ በቀጣይ እንደ ባህል አልባሳት፣ ቀበቶ፣ ከረባትና ሌሎች ምርታቸውን ለውጪ ገበያ ለማቅረብ አቅደው የማሽነሪ ግዥ ለመፈጸም መዘጋጀታቸውን ጠቁማለች፡፡ ''ሁሉ ከሰራ በሀገር ውስጥ መለወጥ ሰለሚችል ስደት ተገቢ አለመሆኑን ሁሉም ተረድቶ ለመስራት መጣር አለበት'' ብላለች፡፡    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም