በላሙ ኮሪደር ባለስልጣን የሚመራ ልዑክ ኢትዮጵያን ይጎበኛል

93

ሚያዝያ 27/2011 በኬንያ የላሙ ኮሪደር ልማት ፕሮጄክት የቦርድ አባላት በኢትዮጵያ ጉብኝት ያደርጋሉ። 

የላሙ ፕሮጀክት ከአፍሪካ የኢኮኖሚ ውህደት ማስፈጸሚያ ፕሮጀክቶች አንዱ ሲሆን በተለይም የምስራቅ አፍሪካን በኢኮኖሚው ለማስተሳሰር ታልሞ በመሰራት ላይ ያለ ግዙፍ ፕሮጀክት ነው።

ከፕሮጀክቶቹም ትልቁ የላሙ ወደብ ግንባታ ሲሆን በግንባታው ሶስት የመርከብ ተርሚናሎች ግንባታ እየተፋጠነ መሆኑና አንደኛው በመጪው ሰኔ እንደሚጠናቀቅ መገለጹ ይታወሳል።

ፕሮጀክቱ የኢትዮጵያንና የኬንያን ታሪካዊ ግንኙነት ወደ ላቀ ኢኮኖሚያዊ ግንኙነት እንደሚያሳድግም ተስፋ ተጥሎበታል።

ይህን ለማሳካትም የሁለቱ አገራት መንግስታት ፕሮጀክቱን በትኩረት እየተከታተሉት ይገኛሉ።

የዚሁ እንቅስቃሴ አካል የሆነውና በኬንያ የላሙ ኮሪደር ልማት ፕሮጄክት የቦርድ አባላት የልዑካን ቡድን በኢትዮጵያ ጉብኝት እንደሚያደርጉ ነው የተገለጸው።

በላሙ ፕሮጄክት ዳይሬክተር ጄኔራል ሲልቪስተር ኪሲኩ የሚመራው ይህ ቡድን ከሚያዝያ 26 እስከ ግንቦት 2 ቀን 2011 ዓ.ም በኢትዮጵያ በሚኖረው ቆይታ ከተለያዩ የመንግስት አካላት ጋር ውይይት ያደርጋል።

በዚህ ጉብኝት ላይም 30 የሚሆኑ የቡድኑ አባላት የላሙ ኮርደር ልማት የደረሰበትን ደረጃ በተመለከተ ከኢትዮጵያ የመንግስት ኃላፊዎች ጋር የሚወያዩ ሲሆን በተጨማሪም በኬንያ በኩል የደረሰበትን ደረጃ በተመለከተም ማብራሪያ ያቀርባሉ።

ከኬንያ የውጭ ጉዳይ የኢኮኖሚ ልማት ሚኒስቴር፣ ከላሙ ጉዳዮች ባለስልጣንና ከሌሎች ተቋሞች ኃላፊዎችን ያከተተው ይህ ቡድን የአገራችን የኢንዱስትሪ ፓርኮችን እንደሚጎበኝም ተገልጿል።

በኬንያ የኢ.ፌ.ዲ.ሪ ባለሙሉ ስልጣን አምባሳደር መለስ ዓለምና የላሙ ፕሮጄክት ዳይሬክተር ጄኔራል በቅርብ በሚመረቀው የላሙ ወደብ የመርከቦች ማቆያ ዙሪያ ተወያይተዋል።

አምባሳደር መለስ በውይይታቸው ወቅት የላሙ ወደብ ልማት የአካባቢው አገሮች ኢኮኖሚ ለማስተሳሰር አስፈላጊ በመሆኑ ኢትዮጵያ ለስኬታማነቱ እንደምትሰራ ገልፀውላቸዋል፡፡

ዳይሬክትር ጄኔራሉ በበኩላቸው በላሙ ሶስት የመርከቦች ማቆያ ስራ እየተፋጠነ መሆኑን ገልፀው ይህም የኢትዮጵያን ተጠቃሚነት ያረጋግጣል ብለዋል።

የላሙ ፕሮጄክት ኢትዮጵያና ኬንያ በአፍሪካ ቀንድ የኢኮኖሚ ውህደት ጉልህ ሚና እንደሚጫወት እንደሚያደርግ የገለጹት ዳይረክተሩ ለዚህም የኬንያ መንግስት ቁርጠኛ መሆኑን ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም