የቱሪስት መዳረሻ ቦታዎች በቂ መሰረተ ልማት ሊኖራቸው ይገባል

172
አዳማ ግንቦት 28/2010 ሀገሪቱ ያላትን የቱሪዝም ሀብት በአግባቡ ጥቅም ላይ ለማዋል የመስህብ መዳረሻ ቦታዎች በቂ መሰረተ ልማት ሊኖራቸው ይገባል ተባለ፡፡ የኢትዮዽያ ቱሪዝም ድርጅት ከኦሮሚያ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ጋር በመተባበር ያዘጋጀው የማስፈጸም አቅም ግንባታ ስልጠና ዛሬ በአዳማ ከተማ ተጀምሯል። በዚህ ወቅት የድርጅቱ  ምክትል ዳይሬክተር ጀነራል ረዳት ፕሮፌሰር የቻለ ምህረት ለኢዜአ እንዳሉት  ሀገሪቱ  ሰፊ የሆነ ተፈጥሮዊና ሰው ሰራሽ የቱሪዝም ሃብት ቢኖራትም በአግባቡ እየተጠቀመችበት አይደለም። ለዘርፉ ማነቆ ከሆኑባት  መካከል በበርካታ የቱሪስት መዳረሻዎች አካባቢ በቂ የመሰረተ ልማት አለመኖር ይጠቀሳል። የሰለጠነና ብቃት ያለው የሰው ኃይል እጥረትም ዘርፉን እየተፈታተነ መሆኑን የተናገሩት  ረዳት ፕሮፌሰሩ በዘርፉ ያሉትን ችግሮች ለመፍታት መንግስት፣ባለሀብቱና ህዝቡ በትኩረት በመስራት ማመቻቸት እንዳለባቸው  አመልክተዋል። ድርጅቱ እየተገባደደ ባለው የበጀት ዓመት በስድስት ፓርኮች ውስጥ ቱሪስቶች መሰረታዊ አገልግሎቶችን የሚያገኙባቸው የጎብኚዎች ማዕከላት  እያስገነባ መሆኑን ጠቁመዋል። ስልጠናው የተዘጋጀውም በቱሪስት መዳረሻ ቦታዎች  አስፈላጊነትና አልምቶ ማመቻቸት በሚቻልበት ግንዛቤ ለመፍጠር ነው፡፡ እንዲሁም ከመጪው ዓመት ጀምሮ ሀብቱን በሚገባ ጥቅም ላይ ለማዋል  ከክልሎች ጋር ተባብሮ ለመስራት የሚቻልበትን ሁኔታ ለማመቻቸት ጭምር እንደሆነም ረዳት ፕሮፌሰሩ  አስረድተዋል። በ2010 የበጀት ዓመት የመጀመሪያዎቹ ዘጠኝ ወራት ከ700 ሺህ የሚበልጡ ቱሪስቶች ሀገሪቱን መስህቦች መጎብኘታቸውም ጠቁመዋል። የኦሮሚያ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ምክትል ኃላፊ ዶክተር ተሾመ ከበደ በበኩላቸው በክልሉ ለቱሪዝም ልማት አመቺ የሆኑ ሰፊ ተፈጥራዊ፣ ታሪካዊና ባህላዊ ሀብቶች እንዳሉ ገልጸዋል። ለቱሪዝም ልማቱ ከዋሉት ውስጥ የስምጥ ሸለቆ ሐይቆች፣ፏፏቴዎች፣ዋሻዎች፣የገዳ ስርዓት፣የኢሬቻ በዓል፣ዕደ ጥበብ ስራዎችን ጠቅሰዋል። ቢሮው የቱሪዝም ዘርፉን ይበልጥ በተቀናጀ መንገድ ለመምራት የሚያስችለውን የአስር ዓመታት የቱሪዝም ማስተር ፕላን ማዘጋጀቱንም ዶክተር ተሾመ ተናግረዋል። "ማስተር ፕላኑ በክልሉ ያሉትን የቱሪዝም ሀብቶችን በመዳሰሰ መሰረታዊ አቅርቦቶችን በማሟላት ዘርፉን ለማልማትና ለማበልጸግ ይረዳል" ብለዋል።  ስልጠናው ምርጥ የቱሪስት መዳረሻዎች ተመቻችተው  ዘርፉን ለማሳደግ እየተደረገ  ያለውን ጥረት ለማጎልበት  አቅም እንደሚፈጥርም  አመልክተዋል። ሀገሪቱ በቱሪዝም ዘርፍ መሳተፍ ከጀመረች ከ50 ዓመታት በላይ ብታስቆጥርም ዘርፉን ለማሳደግ የሚችል የበቃ የሰው ሃይል እጥረትና ደረጃውን የጠበቀ አገልግሎት አሰጣጥ ውስንነቶች እንዳሉ የተናገሩት ደግሞ የኢትዮዽያ ቱሪዝም ድርጅት የህዝብ ግንኙነትና ኮሙዩኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ጌትነት ይግዛው ናቸው፡፡ በዚህም  ምክንያት  መንግስትና ህዝቡ ከዘርፉ ተገቢውን ጥቅም እንዳላገኙ ጠቁመው  የቱሪዝም ኢንዱስትሪው እንዲያብብ ሃገራዊ ንቅናቄ እንደሚያስፈልግ ነው  የገለጹት፡፡  ለአምስት ቀናት በተዘጋጀው የስልጠናው መድረክ በክልሉ ከሚገኙ ዞኖችና ዋና ዋና ከተማዎች የተወጣጡ የዘርፉ ስራ ኃላፊዎችና ባለሙያዎች እየተሳተፉ ነው፡፡ ተሳታፊዎቹ በቆይታቸውም ቱሪዝም መዳረሻ ፣ምርትና አገልግሎት፣ ቱሪዝም ማስተር ፕላን በሚሉት ርዕሶች  ዙሪያ  ገለጻ ተደርጎላቸው እንደሚወያዩ ይጠበቃል፡፡        
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም