የአለም ባንክ በአውሎ ንፋስ ለተጠቁ የደቡብ አፍሪካ ሃገራት 545 ሚሊየን ዶላር ሰጥቷል

111

ሚያዚያ 27/2011 የአለም ባንክ ከግማሽ ቢሊዮን ዶላር በላይ በአውሎንፋስ ለተጠቁት የደቡብ አፍሪካ ሃገራት ድጋፍ አድርጓል ፤የአለም ባንክ መሪ በአውሎ ንፋስ ክፉኛ የተጠቃችውን ሞዛምቢክ ከጎበኙ በኋላ  ድጋፉ እንደሚቀጥል ተናግረዋል፡፡

የሲጂቲኤን አፍሪካ እንደዘገበው  አጠቃላይ 545 ሚሊየን ዶላር የተደረገው ድጋፍ ባለፈው መጋቢት ወር “አይዳይ” አውሎ ንፋስ ጉዳት ላደረሰባቸው ለሞዛምቢክ ፣ዝምባብዌ እና ማላዊ  ነው፡፡

“አውሎንፋሱ የከፋ ጉዳት በማድረስ በሚሊየን የሚቆጠሩ ዜጎችን አጥቅቷል” ያሉት የአለም ባንክ ግሩፕ ፕሬዝዳት ዴቪድ ማልፓስ  በአውሎ ንፋስ የተጠቃችውን የሞዛምቢኳን  ቤሪያ ከተማ ከጎበኙ በኋላ ነው፡፡

“ይህ አስከፊ ሁኔታ እንደገናም ኬንዝ በተሰኘ አውሎ ንፋስ ተደግሟል”ያሉት ፕሬዝዳንቱ ሞዛምቢክ ከመጀመሪያው አውሎ ንፋስ ከ6 ሳምንት በኋላ በድጋሚ ተጠቅታለች ብለዋል፡፡

አይዳይ የተሰኘው አውሎ ንፋስ እኤአ መጋቢት 14/2019  የወደብ ከተማዋን ቤሪያን እና አካባቢውን በሃይለኛ ጎርፍ በማጥለቅለቅ ለ600 ሰዎች ህልፈት ምክንያት ሆኗል፡፡

ከሳምንታት በኋላም ኬንዝ የተሰኘው አውሎ ንፋስ  በሃገሪቱን ሰሜናዊ አቅጣጫ  ከቤሪያ 1ሺህ ኪሎ ሜትር እርቀት  ለ41 ሰዎች ህልፈት ምክንያት ሆኗል፡፡

ሞዛምቢክ 350 ሚሊየን ዶላር ያገኘች ሲሆን በአውሎንፋሱ ጉዳት ለደረሰባቸው የውሃ መስመሮች፣መሰረተልማቶችና ለበሽታ መከላከል ስራዎች የምታውለው ይሆናል፡፡

ማላዊ 120 ሚሊየን ዶላር ያገኘች ሲሆን አውሎ ንፋሱ ጉዳት ላደረሰበት የግብርናና የመሰረተ ልማት መልሶ ማገገም ይውላል፡፡

ዝምባብዌ 75 ሚሊየን ዶላር የደረሳት ሲሆን በአውሎ ንፋሱ ለተጠቁ ሰዎች የማህበራዊ ደህንነት ፕሮግራም የምታውለው መሆኑን የገለፀው የሲጂቲኤን አፍሪካ ዘገባ ነው፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም