በመንገድ ላይ ጉዳት የሚያደርሱ አካላትን ተጠያቂ ማድረግ እንደሚያስፈልግ ተጠቆመ

81
አዲስ አበባ ግንቦት 28/2010 የመንገድ ደህንነትን ለመጠበቅ በመንገድ መሰረተ ልማት ላይ ጉዳት የሚያደርሱ አካላትን ተጠያቂ ማድረግ ያስፈልጋል ሲሉ የዘርፉ ባለድርሻ አካላት ገለፁ። የአዲስ አበባ መንገዶች ባለስልጣን ከፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ጋር በመተባበር የመንገዶች የውሃ ማስተላለፊያ መስመርን በተመለከተ ከባለድርሻ አካላት ጋር ምክክር አድርጓል። ምክክር መድረኩ የተገኙት ባለድርሻ አካላት በመንገድ መሰረተ ልማት ላይ የሚደርስ ጉዳትን ለመቀነስ ህጉ ሊጠናከርና ተግባራዊነቱ ትኩረት ሊያገኝ እንደሚገባ አስገንዝበዋል። ከአዲስ አበባ ትራንስፖርት ፕሮግራሞች ማስተባበሪያ ፅህፈት ቤት የመጡት ወይዘሮ ካሳዬ እምሬ መንገድ የሁሉም ሃብት በመሆኑ የሁሉንም የህብረተሰብ ክፍል ግንዛቤ ማሳደግ እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል። የመንገድ መሰረተ ልማት ላይ የሚደርሰውን ጉዳት ለመቀነስ በባለድርሻ አካላት በሁሉም ደረጃ መቀናጀት እንደሚገባቸውና ተጠያቂነትን ማስፈን እንደሚያስፈልግ ጠቁመዋል። በመንገድ ላይ ጉዳት የሚያደርሱ አካላት ሲኖሩ ተጠያቂ የሚያደርግ ጠንከር ያለ ህግ ሊኖር እንደሚገባና ወደተግባር ለመቀየር በትኩረት ሊሰራ እንደሚገባ ተናግረዋል። የባለስልጣኑ የህዝብ ክንፍ አባል የሆኑት አቶ ነቢል መሀመድ እንደተናገሩት፤ በከፍተኛ ወጪ የሚገነቡ መንገዶች ተበላሽተው ለተጨማሪ ወጪ እንዳይዳረጉ በመንገድ ደህንነት ላይ የሚከሰቱ ችግሮች በአፋጣኝ ሊፈቱ ይገባል። 'መንገዶች የመኪና ማጠቢያ እየሆኑ ነው። ህብረተሰቡ ለፅዳት ያለው ግንዛቤ አናሳ በመሆኑ ሽንት ቤትን ከመንገድ ፍሳሽ ማስተላለፊያ ቱቦ ጋር እያገናኘ ነው' በማለት የባህሪ ለውጥ እንዲመጣ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራ መጠናከር እንዳለበት ተናግረዋል። 'የመንገዶች የውሃ ማስተላለፊያ መስመር መሰረተ ልማት ደህንነትና እንክብካቤ' በሚል በባለስልጣኑ በቀረበ ፅሁፍ እንደሚያሳየው፤ የመንገድ ፍሳሽ መሰረተ ልማት መንገድ ላይ የሚፈስ ውሃ ወደ ወንዝ እንዲገባና የመንገድ መሰረተ ልማት በጎርፍና በውሃ እንዳይጎዳ ያደርጋል። የመንገድ ፍሳሽ መሰረተ ልማት መንገዶች ረጅም እድሜ እንዲያገለግሉና ለእግረኛና ለተሽከርካሪ ምቹ የሆነ የትራፊክ ፍሰት እንዲኖር ያስችላል። በህብረተሰቡና ባለድርሻ አካላት የግንዛቤ ችግር መስመሮቹን ከሽንት ቤት ጋር ማገናኘት፣ የፍሳሽ መግቢያውን በቆሻሻ መዝጋት፣ የግንባታ ግብዓቶችን ወደ መስመሮቹ መግባትና የመሳሰሉት ለመንገዶች የውሃ ማስተላለፊያ መስመር መበላሸት መንስኤ መሆኑም በፅሁፉ ተብራርቷል። በዚህ ሳቢያ ጎርፍ፣ የትራፊክ ፍሰት መስተጓጎልና የመንገድ ብልሽት እንደሚከሰት ተጠቁሟል። የመንገድ ፍሳሽ መስመሮችን በባለስልጣኑና ህብረተሰቡ ተሳትፎ ማፅዳት፣ የኀብረተሰቡን ግንዛቤ ማሳደግና ከባለድርሻ አካላት ጋር ተቀናጅቶ መስራት ለችግሩ መፍትሄ እንደሚሆን ተነግሯል። የአዲስ አበባ መንገዶች ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ኢንጂነር ሃብታሙ ተገኝ፤ ባለስልጣኑ አደረጃጀቱን ለማስተካከልና የህብረተሰቡን ግንዛቤ ለማሳደግ እየሰራ ነው። ተጠያቂነትን ለማምጣትም በመንገድ መሰረተ ልማት ላይ ጉዳት የሚያደርሱ አካላት የሚጣልባቸውን ቅጣት ለማጠናከርና ከህግ አስፈፃሚ አካላት ጋር ተቀናጅቶ ለመሄድ እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል። ከባለድርሻ አካላት ጋር የመግባቢያ ሰነድ ተፈራርሞ መስራት ከተጀመረ ወዲህ ተቀናጅቶ ለመስራት የሚደረገው ጥረት እየተሻሻለ መምጣቱን ተናግረዋል። ባለስልጣኑ ከ2009 ዓ.ም ጀምሮ ለመንገዶች የውሃ ማስተላለፊያ መስመር ስራ 81ነጥብ6 ሚሊዮን ብር ወጪ እንዳደረገ ከባለስልጣኑ የተገኘ መረጃ ያሳያል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም