'ኢትዮጵያ የዓለም የፕሬስ ነጻነት ቀን ማስተናገዷ በአገሪቱ የፕሬስ ነጻነትን ለማሳደግ ያግዛታል'-የአክሱም ዩኒቨርሲቲ ምሁራን

57

አክሱም ሚያዝያ 26 /2011 ኢትዮጵያ የዓለም የፕሬስ ነጻነት ቀን ማስተናገዷ በአገሪቱ የፕሬስ ነጻነትን ለማሳደግ ያግዛታል ሲሉ የአክሱም ዩኒቨርሲቲ የጋዜጠኝነትና ኮሙኒኬሽን ምሁራን ተናገሩ።

የፕሬስ ነጻነት መሻሻል በመርህ ለመመራትና ሙያዊ ኃላፊነት ለማስቀጠል የመገናኛ ብዙኃን ተቋማትና ባለሙያዎች በኃላፊነት መንፈስ እንዲሰሩም ተጠይቋል።

ምሁራኑ ከኢዜአ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ እንዳመለከቱት ቀኑ በአገሪቱ መከበሩ በአገር ውስጥ የመገናኛ ብዙኃንን ነጻነት በተሞላበት መንገድ እንዲንቀሳቀሱ ያደርጋል።

መምህርት ዙሃራ መሐመድ ኢትዮጵያ ዘንድሮ በዓለም አቀፍ ደረጃ የፕሬስ ነጻነት ቀንን እንድታከብር የተሰጣት ዕድል በአገር ውስጥ የፕሬስ ነጻነት ለማሳደግ ያስችላል ብለዋል።

ኢትዮጵያ ቀኑን እንድታስተናግድ የተመረጠችው ለመገናኛ ብዙኃን ነጻነት መረጋገጥ ባደረገችው ጥረትና መሻሻል በማሳየቷ መሆኑንም አውስተዋል።

የታሰሩ ጋዜጠኞች እንዲፈቱና ለመገናኛ ብዙኃን የተሰጠው ነጻነት በዓለም አቀፍ ደረጃ እንድትታወቅና ደረጃዋን እንድታሻሽል ረድቶታል ሲሉም አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።

በአገሪቱ በመጣው የፕሬስ ነጻነት መሻሻል ሙያን መሠረት ባደረገ፣ በአግባቡና በኃላፊነት ሊመራ እንደሚገባም መምህርት ዙሃራ ጠቁመዋል።

የአገሪቱ መገናኛ ብዙኃን በስመ ነጻነት ግጭትን፣መከፋፈልንና የአንድ ቡድን ፍላጎት መሠረት ያደረጉና ሚዛናዊ የጎደላቸው ዘገባዎና ፕሮግራሞች እያስተላለፉ ነው ያሉት መምህሯ፣ነጻነቱን በአግባቡ ልንጠቀምበት ይገባል ሲሉም መክረዋል።

መገናኛ ብዙኃን ብሄራዊ መግባባትን ለመፍጠርና አንድነት ለማጠናከር እንዲሰሩም  አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።

ሌላኛው በዩኒቨርሲቲው መምህር አቶ ጽጋቡ ሞትባይኖር እንዳሉት ጋዜጠኞች በሙያቸው ኃላፊነት በተሞላው መንገድ በመዘገብ ዜጎች ተአማኒና ትክክለኛ መረጃ እንዲያገኙ ብሎም ለሰላምና ዴሞክራሲ መስፈን ሊሰሩ ይገባል።

ብሄርን ከብሄር ለማጋጨት፣ የጥላቻ ንግግርን በማስተናገድና አንድን የፖለቲካ ድርጅት በመደገፍ ወይም በመቃወም ኃላፊነት የጎደለው የተሰማሩ የክልልና የፌዴራል መንግሥታት ነጻነት ገደብ እንዳለው ሊያውቁ ይገባል ብለዋል።

በአንዳንድ መገናኛ ብዙኃን የጋዜጠኝነትና ሥነ ምግባርን መሠረት ያላደረጉ ተግባራት እየተከናወኑ  መሆናቸውን የተናገሩት ምሁር፣ መንግሥት ነጻነታቸው ሳይነካ ትክክለኛ አቅጣጫ እንዲይዙና በኃላፊነት መንፈስ እንዲሰሩ ድጋፍ እንዲያደርግላቸው ጠይቀዋል ።

የመገናኛ ብዙኃን ተቋማትና ባለሙያዎቹ ነጻነታቸውን ተጠቅመው ለአገር ግንባታ፣ ለሰላምና ልማት እንዲያውሉት  አቶ ጽጋቡ አመልክተዋል።

የዓለም የፕሬስ ቀን በዚህ ሣምንት በአዲስ አበባ  ለ26ኛ ጊዜ መከበሩ ይታወሳል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም