ጣሊያን ለህክምና ዘርፍ የምታደርገው ድጋፍ ተግባር ላይ እየዋለ መሆኑን እንዳረጋገጡ የአገሪቷ ፓርላማ አባላት ተናገሩ

101

  አዲስ አበባ  ሚዝያ  26/2011 ጣሊያን ለኢትዮጵያ ለህክምናው ዘርፍ የምታደርገው ድጋፍ ተግባር ላይ መዋሉን እንዳረጋገጡ የአገሪቷ የፓርላማ አባላት ተናገሩ።

በኢትዮጵያ ይፋዊ የስራ ጉብኝት እያደረጉ የሚገኙት የጣሊያን የፓርላማ አባላት የመድሃኒት አቅራቢ ኤጀንሲን የአዳማ ቅርንጫፍ ጎብኝተዋል።

ለፓርላማ አባላቱ ኢትዮጵያ ከጣሊያንን እና ከተለያዩ ለጋሽ ድርጅቶች የምታገኘውን ድጋፍ ለመድሃኒት ክምችት፣ አስተዳደር፣ ተደራሽነት፣ ዘመናዊ አሰራርን ለመዘርጋትና የሰው ሃይል ማብቃት እያዋለችው መሆኑን ገለጻ ተደርጎላቸው።

የአባላቱ መሪ የጣሊያን የፓርላማና የውጭ ጉዳይ ኮሚሽን አባል ያና ኢም እንደገለጹት፤ የጉብኝታቸው ዓላማ ኢትዮጵያ የሚደረግላትን ድጋፍ በተጨባጭ ተግባር ላይ እያዋለችው መሆኑን በማረጋገጥ ቀጣይ ድጋፎች እንዲጠናከሩ ለማድረግ ነው።

በጉብኝታቸው ጣሊያን በግሎባል ፈንድ በኩል ለክትባት መድሃኒት፣ ለአሰራር ማሻሻያና ለአቅም ግንባታ ያደረገችው ድጋፍ ተጨባጭ ለውጥ እያመጣ መሆኑን ተገንዝበዋል።

ዘመናዊ የመድሃኒት የክምችት አስተዳደር ስርዓት ለመዘርጋት እየተሰራ ያለውን ተግባር  በጥሩ ጎኑ አንስተዋል።

የፓርላማ አባላቱ ወደ ጣሊያን በሚመለሱበት ወቅትም መንግስታቸው በግሎባል ፈንድ በኩል ለጤናው ዘርፍ እያደረገ ያለው ድጋፍ ውጤት እያስገኘ መሆኑን በማስረዳት "ድጋፋ እንዲጠናከር እንሰራለን" ብለዋል።

በኢትዮጵያ እየመጣ ያለውን ለውጥ ተከትሎ በጤናው ዘርፍ ብቻም ሳይሆን በተለያዩ የኢንቨስትመንት ዘርፎች የጣሊያን ባለሃብቶች በኢንቨስትመንት ላይ መሰማራት እንዲችሉ ያዩትን አመቺ ሁኔታ እንደሚያጋሩም ገልጸዋል።

በመድሃኒት አቅርቦት ኤጀንሲ የአዳማ ቅርንጫፍ ስራ አስኪያጅ አቶ ሰለሞን ንጉሴ በበኩላቸው፤ በድጋፉ አማካኝነት የመድሃኒት አቅርቦት ስርዓትን ቀልጣፋ ለማድረግ ተጠናቀው ወደ አገልግሎት የገቡ ፕሮጀክቶች በተግባር ያመጡትን ለውጥ እንዲገነዘቡት ተደርጓል።

በመጋዘን፤ ክምችትና ስርጭት አስተዳደር የመጡ ለውጦችን ከፓርላማ አባላት ጋር ውይይት መካሄዱን የገለጹት ስራ አስኪያጁ፤ በቀጣይ በዓለም አቀፍ ፈንድ በኩል ድጋፋቸውን በሚያጠናክሩበትን መንገድ ላይ ምክክር መደረጉን አብራርተዋል።

በተለይም ህብረተሰቡ የሚፈልገውን መድሃኒት በሚፈልገው ጊዜ እንዲያገኝና ተደራሽነቱን ለማፋጠን እንዲቻል የተዘረጉ አሰራሮችን መሰረት በማድረግ ለጣሊያን መንግስ ለማስረዳትና ድጋፉ የሚቀጥልበትን ሁኔታ ለማመቻቸት የፓርላማ አባላቱ ቃል ገብተዋል።

እንደ ሥራ አስኪያጁ ገለጻ፤ የማያገለግሉና ጥቅም ላይ የማይውሉ የተበላሹ ህክምና መሳሪያዎችና ጊዜ ያለፈባቸው መድሃኒቶችን ለማስወገድ የሚያገለግሉ ስምንት ማቃጠያዎች ተገንብተዋል።

የጣሊያን መንግስት በክትባት አቅርቦት እያደረገ ያለው ድጋፍ ከፍተኛ ሲሆን፤ አሁን እስከ ወረዳ ያለውን ተደራሽነት እስከ ጤና ኬላ ለማድረስ ድጋፍ እንዲያደርግ ምክክር መካሄዱን ነው የገለጹት።

የክምችት አስተዳደር ስርዓቱ በቴክኖሎጂ የታገዘና ዘመናዊ አሰራርን ለመዘርጋትም ኢትዮጵያ የጀመረችውን ተግባር በሚደግፉበት ሁኔታ ላይ ውይይቱ ማተኮሩንም አውስተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም