የገደብ ተፈናቃዮች ወደ ቄያቸው ተመልሰው በዘላቂነት እንዲቋቋሙ መንግሥት ድጋፍ እንዲያደርግላቸው ጠየቁ

46

ዲላ ሚያዝያ  26/2011  ወደ ቄያቸው ተመልሰው በዘላቂነት እንዲቋቋሙ መንግሥት ድጋፍ እንዲያደርግላቸው በጌዴኦ ዞን የገደብ ወረዳ ተፈናቃዮች ጠየቁ፡፡

መጠለያ ባልተመቻቸበት ሁኔታ ወደ ቄያቸው እንዲመለሱ መወሰኑ ተገቢነት እንደሌለውም ገልጸዋል፡፡

አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ አንዳንድ ተፈናቃዮች እንዳስረዱት ወደ ቀደመው መኖሪያቸው ለመመለስ የሚደረገው እንቅስቃሴ በመንግሥት ሁለንተናዊ ድጋፍ መታገዝ አለበት።

ከተፈናቃዮቹ  መካከል  ወይዘሮ ብርቱካን ሃጂ  መንግሥት የወደመ ሃብት ንብረታቸውን ተክቶ በዘላቂነት የሚቋቋሙበት ሁኔታ ለፈጥርልኝ ይገባል ይላሉ፡፡

ያለበለዚያ በተደጋጋሚ በደረሰባቸው መፈናቀል ለማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ቀውስ ከተዳረጉበት ሁኔታ  እንዳማይወጡ ተናግረዋል፡፡

መጠለያ ባልተሰራበት ሁኔታ ወደ ቄያችን መመለሳቸው ለከፋ ጉዳት ሊዳርጋቸው እንደሚችልም ስጋታቸውን ገልጸዋል። 

በተለይም ላለፉት ሁለት ዓመታት ከትምህርት ገበታቸው ውጭ የሆኑ ልጆቻቸው ወደ ትምህርት የሚመለሱበት መንገድ እንዲመቻችላቸው ጠይቀዋል፡፡

ወይዘሮ ማርታ ክፔ የክረምት ወራት መግባቱን ተከትሎ በመጠለያ ጣቢያ እየጣለ ያለው ዝናብ ኑሮአቸውን አስቸጋሪ እንዳደረገው ይናገራሉ።

በምዕራብ ጉጂ ዞን አንጻራዊ ሰላም በመስፈኑ ወደ ቀድሞው መኖሪያቸው መመለሳቸው ተገቢ ነው ብዬ  አምናለሁ ይላሉ፡፡

ይሁንና በቀርጫ ወረዳ 01 ቀበሌ ከአንድ ዓመት በፈት የፈረሰው ቤታቸው እስካሁን ባለመጠገኑ ተመልሰው ከልጆቻቸው ጋር ለመኖር እንደሚቸገሩ  አስረድተዋል ፡፡

የምዕራብ ጉጂ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ አበራ ቡኖ በበኩላቸው ተፈናቃዮችን ወደ ቄያቸው ለመመለስ ከመግባባት ላይ መደረሱን ገልጸዋል፡፡

በተለይም በቀርጫ ወረዳ የነበሩ ተፈናቃዮች ወደ ቄያቸው መመለስ መጀመራቸውን ተናግረዋል፡፡

ይሁንና በዞኑ ከ26 ሺህ በላይ ቤቶች ላይ ጉዳት በመድረሱ ሁሉንም በአጭር ጊዜ ውስጥ ሰርቶ ለማጠናቀቅ የመንግሥትን አቅም ከመፈታተን ባለፈ ጊዜ አንደሚጠይቅ አብራርተዋል፡፡

የዞኑ አስተዳደር ከየአካበቢው ነዋሪዎች ጋር በመተባበር ለተፈናቃዮቹ  ጊዜያዊ ቤቶችን በመስራት ላይ መሆኑን አስረድተዋል፡

የጌዴኦና የጉጂ ህዝቦች የሚተዋወቁና የሚደጋገፉ በመሆናቸው ተፈናቃዮችን መልሶ ለማቋቋም  በጋራ መስራት እንዳለባቸው አሳስበዋል፡፡

የጌዴኦ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ገዙ አስፋ በበኩላቸው በሁለቱም ወገኖች የሚገኙ ተፈናቃዮችን በአጭር ቀናት ወስጥ ወደ ቄያቸው ለመመለስና በዘላቂነት ለማቋቋም እየተሰራ ነው ብለዋል፡፡

ከጌዴኦ ዞን ከገደብ ወረዳ ሶሰት ቀበሌዎች ተፈናቅለው ወደ ምዕራብ ጉጂ ዞን የሄዱ ዜጎችን ለመቀበል የፈረሱ ቤቶች እድሳትና ጥገና በመከናወን ላይ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም