ህገ-መንግስታዊ ስርዓቱን አጠናክሮ ለማስቀጠል የፍትህ አካላትና አመራሮች ኃላፊነታቸውን በእግባቡ ሊወጡ ይገባል

66
መቀሌ ግንቦት 28/2010 በህዝቦች የጋራ ፍላጎትና ትግል የተረጋገጠውን ህገ-መንግስታዊ ስርዓት አጠናክሮ ለማስቀጠል የፍትህ አካላትና በየደረጃው ያሉ አመራሮች  ኃላፊነታቸውን በአግባቡ እንዲወጡ ተጠየቀ። የፌደሬሽን ምክር ቤት ያዘጋጀውና ከወረዳ እስከ ክልል ለሚገኙ የትግራይ ክልል የፍትህ አካላት፣ የቢሮ ኃላፊዎችና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች የተሳተፉበት የሁለት ቀን የምክክር መድረክ ተጀምሯል። በምክክር መድረኩ ላይ የተገኙት የትግራይ ከልል ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ወይዘሮ ቅዱሳን ነጋ እንዳሉት ህገ -መንግስቱ በአግባቡ ሥራ ላይ ውሏል የሚባለው ለሕዝብና ለአገር በተግባር ሲጠቅም ነው። ህገ መንግስታዊ ስርዓቱ ህዝብና አገርን በአግባቡ ተጠቃሚ ከማድረግ ባለፈ ተጠናክሮ እንዲቀጥል የፍትህ አካላትን ጨምሮ በየደረጃው ያሉ አመራሮች ኃላፊነታቸውን በአግባቡ እንዲወጡ ጥሪ አቅርበዋል። በምክክር መድረኩ በህገ መንግስት ጽንሰ ሀስብና አተረጓጎም፣ በፌዴሬሸን ምክር ቤት አሰራር፣ በፍትህ አካላት የአገልግሎት አሰጣጥና መሰል ጉዳዮች ላይ ውይይት እንደሚደረግም ወይዘሮ ቅዱሳን አመልክተዋል። በፌደሬሽን ምክር ቤት የህገ - መንግስት ትርጉምና ማንነት ጉዳዮች ዳይሬክተርና የመድረኩ አስተባባሪ አቶ ሙልዬ ወለላው በበኩላቸው እንዳሉት ውይይቱ የህግ መንግስት አተረጓጎም እውቀትና ክህሎትን በሚመለከታችው አካላት ዘንድ በማዳበር ቀልጣፋ የፍትህ አገልግሎት ለመስጠት ያለመ መሆኑን ተናግረዋል። በመድረኩ ላይ ከትግራይ ክልል የተለያዩ ቢሮዎች የተውጣጡ የሥራ ኃላፊዎች፣ የፍትህ አካላትና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል ።        
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም