በ80 ሚሊዮን ዶላር የተገነባው መዝናኛ ስፍራ ያለ አገልግሎት 8 ዓመታትን አሳለፈ

190

ሚያዝያ 26/2011 በበሰቃ ሀይቅ ዳርቻ በ80 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር ወጪ በልዩ የኪነ ህንፃ ጥበብ እንደተገነባ የሚነገርለት የመዝናኛ ስፍራ አገልግሎት መስጠት ሳይጀምር ለ8 ዓመታት ባለቤት አልባ ሆኖ በመቆየቱ መልሶ እየፈረሰ ነው ተባለ ።

ልዩ የመዝናኛ ስፍራው ከመተሀራ ከተማ በሶስት ኪሎ ሜትሮች ርቀት ላይ በ143 ሔክታር መሬት ተከልሎ የተገነባ በመሆኑ ከሩቁ ለየት ብሎ ይታያል ።

በውጭ አገር ሰዎች የተገነባ ልዩ የመዝናኛ ስፍራ ነው ሲባል የሰማ እንጂ በእርግጠኝነት  ዝርዝር መረጃ ያለው የከተማው ነዋሪ ማግኘትም አስቸጋሪ ነው ።

ስለሁኔታው ለማወቅ ጉጉት ያደረበት የኢዜአ የጋዜጠኞች ቡድን ከፈንታሌ ወረዳ ኢንቨስትመንትና ከወረዳው የኮሙኒኬሽን ፅህፈት ቤት ሁለት ባለሙያዎችን በመያዝ ወደ ቦታው ያቀና ሲሆን ግንባታው የሚደነቅ ብክነቱ ግን የሚያሳዝን ሆኖ አግኝቶታል።

ወደ ቦታው ለመግባት ሜዳ ሜዳውን እየመረጡና ከፕሮሶፒስ እሾሃማ መጤ አረም ጋር እየታገሉ እንጂ መኪና ሲመላለስበት የነበረው የገጠር መንገድ አገልግሎት ሳይሰጥ ረጅም ጊዜ  ስለሆነው ተመልሶ ጠፍቷል ።

በቦታው በበሰቃ ሀይቅ ዳርቻ እየዋኙ ከሚጫወቱ ጥቂት የአርብቶ አደር ህፃናት ልጆች  በስተቀር አንድም የጥበቃ ሰራተኛ በስፍራው አልነበረም ።

የፈንታሌ ወረዳ ኢንቨስትመንት ፅህፈት ቤት ባለሙያ አቶ ከማል ዑመር እንደሚሉት  ግንባታው በ80 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር ከ1999 ዓም እስከ 2003 ዓ.ም የተከናወነ ሲሆን ባለቤቱም ሶል ጆኦት ሳዑዲ አሜሪካን ኢንቨስትመንት ሃላፊነቱ የተወሰነ የግል ኩባኒያ በሚል የተመዘገበ ነው ።

የሳዑዲ አረቢያ ተወላጁ የኩባኒያው ባለቤት በ2003 ዓ.ም የበሰቃ ሀይቅ የውሃ መጠኑ  ጨምሮ ወደ መዝናኛ ስፍራው በመግባት በግንባታው ላይ ጉዳት በማድረሱ ተበሳጭተው አካባቢውን ለቀው በመሄዳቸው ግንባታው ሙሉ በሙሉ ሳይጠናቀቅና አገልግሎት መስጠት ሳይጀምር መቅረቱን ባለሙያው ተናግረዋል ።

በጊዜ ሒደት ባለሃብቱ እዛው ሀገራቸው ላይ እንደሞቱ የተሰማ ሲሆን ህጋዊ ወራሾች የሆኑ ቤተሰቦቻቸው ስራውን ለማስቀጠል ፍላጎት እንዳላቸው ከአንድ ወር በፊት ለመንግስት አሳውቀው እንደተፈቀደላችው አቶ ከማል አስረድተዋል ።

ግንባታው ከመቋረጡ በፊት አርብቶ አደሮችን ጨምሮ 300 ለሚሆኑ የአካባቢው ነዋሪዎች የስራ እድል የፈጠረ ነበር ተብሏል ።

ወጣቱ ዓሳ አጥማጅ ዴቪድ ብርሃኑ በመዝናኛ ስፍራው የሚገኘውን አንዱን ማማ መኖሪያው አድርጎ እየተጠቀመበት መሆኑን ይገልፃል ።

ወጣቱ ተወልዶ ያደገው በመተሃራ ከተማ ቀበሌ 01 ሲሆን አሁን ግን ወደ ከተማ የሚወጣው ያጠመደውን የዓሳ ምርት ለመሸጥ እንጂ ውሎና አዳሩን በመዝናኛ ስፍራው ውስጥ አድርጓል ።

“ባለሃብቱ ጥሩ ሰው ነበሩ ። ለበርካታ ወጣት አርብቶ አደሮች የስራ እድል በመፍጠር ተጠቃሚ አድርገውም ነበር ።  አካባቢውን ለቀው ከሔዱ በኋላ ብዙ ንብረት ተዘርፏል ። ግንባታው አገልግሎት ሳይጀምር መልሶ እየፈረሰ በመሆኑ ዘላቂ መፍትሄ ቢበጅለት መልካም ነው” የሚል አስተያየት ሰጥቷል ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም