ፍትሀዊ ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ ያልተማከለ የበጀት ክፍፍል ሥርአትን ማጎልበት እንደሚገባ ተጠቆመ

77
  ሀዋሳ  ግንቦት 28/2010 በክልሎች መካከል ፍትሀዊ ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ በድጎማ በጀት፣ በወጪና በጋራ ገቢ ላይ ያልተማከለ የበጀት ክፍፍል ሥርአትን ማጎልበት እንደሚገባ ተጠቆመ ። የፌዴሬሽን ምክር ቤት ከፎረም ኦፍ ፌዴሬሽን ጋር በመቀናጀት በድጎማ በጀት፣ በጋራ ገቢና ወጭ ክፍፍል ላይ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቋሚ ኮሚቴዎች አባላት ለሁለት ቀናት በሃዋሳ ከተማ ስልጠና ሰጥቷል፡፡ የፌዴሬሽኑ ምክር ቤት ምክትል አፌ ጉባኤ አቶ መሀመድ ረሺድ በእዚህ ወቅት እንደተናገሩት ምክር ቤቱ የፌዴራል መንግስት ለክልሎች የሚሰጠውን የድጎማ በጀት ይወስናል። በተጨማሪም የፌዴራልና የክልል መንግስታት የጋራ ገቢዎች የሚከፋፈልበትን የክፍፍል ቀመር ከመወሰን በሻገር የፌዴራል የመሠረተ ልማት ስርጭት ፍትሃዊነት የማረጋገጥ ኃላፊነት ተጥሎበታል፡፡ በመሆኑም በአገሪቱ ፍትሃዊና እኩል ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ በድጎማ በጀት፣ በወጭና በጋራ ገቢ ክፍፍል ላይ የተጀመረውን ያልተማከለ የበጀት ክፍፍል ሥርአት ማጎልበት ይገባል ብለዋል፡፡ እስካሁንም ምክር ቤቱ የድጎማ፣ የገቢና ወጪ በጀት ቀመር በመወሰን ዘጠኝ የድጎማ በጀትና አንድ የጋራ ገቢ ማከፋፈያ ቀመር በማዘጋጀት ተግባራዊ ማድረጉን አስረድተዋል፡ በቅርቡም የፌዴራል የመሠረተ ልማት ስርጭት ፍትሀዊነት በማጥናት ችግሮችን የለየ ሲሆን ተቋማት በቀጣይ መስራት የሚገባቸውን መሠረታዊ አቅጣጫ ማስቀመጡንም ተናግረዋል፡፡ ፌደሬሽኑ የሚያከናውናቸው ተግባራት ያለባለድርሻ አካላት ንቁ ተሳትፎ ከግብ አይደርሱም ያሉት አቶ መሀመድ፣ ከህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ጋር የነበራቸው ቅንጅት በቂ እንዳልነበረ ገልፀዋል፡፡ ያለውን የቅንጅት ውስንነት ለመቅረፍ የፌዴሬሽን ምክር ቤት ከፎረም ኦፍ ፌዴሬሽን ጋር በመተባበር በድጎማ በጀት፣ በጋራ ገቢና ወጪ ክፍፍል ላይ ለምክር ቤቱ ቋሚ ኮሚቴዎች አባላት ስልጠናውን ማዘጋጀቱን አስረድተዋል። እንደ ምክትል አፈጉባኤው ገለጻ በስልጠናው ላይ የገቢዎች፣ የወጪ አስተዳደርና የበጀት ቋሚ ኮሚቴ አባላት ተሳታፊ ሆነዋል። በመድረኩም ባልተማከለ የበጀት ክፍፍል ሥርአት ጽንሰ ሀሳብና በኢትዮጵያ ያለውን ወቅታዊ የበጀት ክፍፍል ቀመር አስመልክቶ ከፌዴሬሽን ምክር ቤትና ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በመጡ ምሁራን ሰነዶች ቀርበው ውይይት ተደርጎባቸዋል። የፎረም ኦፍ ፌዴሬሽን የምስራቅ አፍሪካ ሪጅናል ዳይሬክተር አቶ ማዕረጉ ሀብተማርያም በበኩላቸው ስልጠናው በፌዴራል መንግስት የሀብት ክፍፍል ምን እንደሚመስልና ያለበትን ደረጃ በመለየት የማሻሻያ ስራዎችን ለመስራት ያለመ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ቀመሩ ከወቅታዊ፣ ከተግባር አፈጻጸምና ከህግ አንጻር ውስንነት ያለበት በመሆኑ ችግሮቹን ለመፍታት የአገር ውስጥና የውጭ ባለሙያዎች የተካተቱበት ምሁራን ጥናት በማካሄድ ላይ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡ የፌዴራል መንግስት ለክልሎች የሚሰጠው የድጎማ በጀት ውጤታማና ተጠያቂነት ያለበት እንዲሆን ለማስቻል በሚያስፈልጉ ማዕቀፎች ላይ ውይይት መደረጉን አስረድተዋል። በስልጠናው ላይ የተሳተፉት በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የበጀትና ፋይናንስ ቋሚ ኮሚቴ ምክትል ሰብሳቢ አቶ ነጋልኝ ዮሴፍ በበኩላቸው "ስልጠናው የፌዴራልና የክልል መንግስት ኃላፊነትን ለይተን በእውቀት ላይ የተመሰረተ ክትትል ለማድረግ ያስችለናል" ብለዋል፡፡ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግስት የልማት ድርጅቶች ጉዳይ ቋሚ ኮሚቴ ምክትል ሰብሳቢ አቶ ተክለ ተሰማ በበኩላቸው እንዳሉት የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት የፌዴራል በጀትና ድጎማ በጀትን እንደሚያጸድቅ ገልጸዋል። በመሆኑም በጀት ሲጸድቅና ቀመር ሲወጣ መመዘኛ መርሆዎችን መሰረት በማድረግና የዓለም አቀፍ ተሞክሮና አገራዊ ነባራዊ ሁኔታን በማመዛዘን ለመወሰን ስልጠናው እንደሚያግዛቸው አመልክተዋል፡፡ ስልጠናው ፌዴራሊዝም ስርዓትን የሚከተሉ አገራት የሚተግብሩትን ያልተማከለ የበጀት ክፍፍል ሥርአት በአግባቡ ለመረዳት እንዳስቻላቸውም ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም