በሸገር ደርቢ ኢትዮጵያ ቡና ከቅዱስ ጊዮርጊስ እሁድ ይገናኛሉ

137

አዲስ አበባ ሚያዝያ 25/2011 በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ 23ኛ ሳምንት ጨዋታ በሸገር ደርቢ ኢትዮጵያ ቡና ከቅዱስ ጊዮርጊስ የሚያገናኘው ጨዋታ ይጠበቃል። 

የፕሪሚየር ሊጉ 23ኛ ሳምንት ጨዋታዎች በተያዘላቸው መርሃ ግብር መሰረት ከቅዳሜ እስከ እሁድ በአዲስ አበባና በክልል ከተሞች ይካሄዳሉ።

ቅዳሜ በ9:00 ሰዓት ደቡብ ፖሊስ ከአዳማ ከተማ፣ ደደቢት ከፋሲል ከነማ ክልል ላይ ሲጫወቱ፤ መከላከያ ከባህርዳር ከተማ አዲስ አበባ ስታዲየም በ10:00 ሰዓት ይገናኛሉ።

መቐለ ሰብአ እንደርታ ከስሁል ሽረ፣ ሃዋሳ ከተማ ከሲዳማ ቡና እንድሁም ድሬዳዋ ከተማ ከወላይታ ዲቻ እሁድ በተመሳሳይ 9:00 ሰዓት በክልል ስታዲየሞች የሚደረጉ ጨዋታዎች ናቸው።

ወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርሲቲ ከጅማ አባጅፋር ሰኞ በ9:00 ሰዓት በትግራይ ስታዲየም የሚደረግ ጨዋታ ነው።

በሸገር ደርቢ ኢትዮጵያ ቡና እና ቅዱስ ጊዮርጊስን እሁድ በ10:00 ሰዓት በአዲስ አበባ ስታዲየም የሚያገናኘው ጨዋታ ሰፊ ትኩረት ተሰጥቶታል።

ቅዱስ ጊዮርጊስ የእግር ኳስ ቡድን ከምስረታው አንስቶ በፕሪሚየር ሊግ፣ በጥሎ ማለፍ፣ በሱፕር ካፕ፣ በአሸናፊዎች አሸናፊና በሌሎችም ውድድሮች ከ50 በላይ ዋንጫዎችን በመሰብሰብ ገናና ለመሆን የቻለ ቡድን ነው።

በአንጻሩ የኢትዮጵያ ቡና በኢትዮጵያ ፕሪሚዬር ሊግ ታሪክ አንድ ጊዜ ዋንጫ ያገኘ ሲሆን፤ በጥሎ ማለፍ፣ በአሸናፊዎች አሸናፊና በሱፕር ካፕ ፣ በራን አዌይ ሊግ በርካታ ዋንጫዎችን ማግኘት የቻለ ክለብ ነው፡፡ 

የበርካታ ደጋፊዎች ባለቤት የሆኑት ሁለቱ ቡድኖች በደጋፊዎቻቸው ህብረ ዝማሬና በተለያዩ የድጋፍ ስልቶቻቸው በኢትዮጵያ እግር ኳስ ላይ የሊጉ ድምቀት ስለመሆናቸው አያጠያይቅም።

በዚህም በሊጉ ሁለቱን ክለቦች የሚያገናኘው ጨዋታ በበርካታ ስፖርት ቤተሰቦች ዘንድ እንዲጠበቅ ያደርገዋል።

ሁለቱ ቡድኖች የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ እንደ አዲስ ከተጀመረ ከ1991 ወዲህ 38 ጊዜ የተገናኙ ሲሆን፥ ቅዱስ ጊዮርጊስ 18 ጊዜ እንዲሁም ኢትዮጵያ ቡና 6 ጊዜ ድል ቀንቷቸዋል።

በ14 ጊዜ  እርስ በርስ ያደረጓቸውን  ጨዋታዎች ደግሞ  በአቻ ውጤት ማጠናቃቸውን መረጃዎች ያመላክታሉ።

የዘንድሮውን የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ መቐለ ሰብአ እንደርታ በ45 ነጥብ ሲመራ፣ ፋሲል ከነማ፣ ቅዱስ ጊዮርጊስና ሲዳማ ቡና ከሁለት እስከ አራት ያለውን ደረጃ ይዘው ይከተላሉ።

ደቡብ ፖሊስ፣ ስሁል ሽረ እና ደደቢት ደግሞ በሊጉ ግርጌ ከ14 እስከ 16 ደረጃ ላይ በመቀመጥ ወራጅ ቀጠና ውስጥ ይገኛሉ።

ኮከብ ግብ አግቢነቱን የመቐለ ሰብአ እንደርታው አማኑኤል ገብረሚካኤል በ13 ገሎች ሲመራ አዲስ ግደይ ከሲዳማ ቡና እንዲሁም ምንይሉ ወንድሙ ከመከላከያ በ12 እና በ13 ጎሎች ይከተላሉ። 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም