በቤንሻንጉል ጉሙዝና አማራ ክልሎች ሰሞኑን የተከሰተውን ግጭት ለማርገብ የሁለቱ ክልሎች አመራሮች በጋራ እየሰሩ እንደሆነ ተገለጸ

105

አዲስ አበባ ሚያዝያ 25/2011 በቤንሻልጉል ጉሙዝና አማራ ክልሎች ሰሞኑን የተከሰተውን ግጭት ለማርገብ የሁለቱ ክልሎች አመራሮች በጋራ እየሰሩ እንደሆነ የአማራ ክልል አስታወቀ።

በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት መተከል ዞን ዳንጉር ወረዳ የተከሰተውን ግጭት በማስመልከት መግለጫ የሰጡት የአማራ ክልላዊ መንግስት የኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ኃላፊ አቶ አሰማኸኝ አስረስ ግጭቱን ለማርገብ በሁለቱ ክልሎች አመራሮች በኩል የተለያዩ ተግባራት እየተከናወነ መሆኑን ተናግረዋል።

ሚያዚያ 17 ቀን 2011 በወረዳው በሁለት ሰዎች መካከል በተፈጠረ ግጭት አንድ የጉሙዝ ብሔረሰብ አባል ህይወቱ ማለፉን አስታውሰዋል።

ይህንን ተከትሎ በነበሩት ቀናት በተለያዩ ወረዳዎችና ቀበሌዎች የገዳዩ ቤተሰቦችና ወገኖች ናቸው በተባሉ ሰዎች ላይ ጉዳት መድረሱን ገልጸዋል።

በዚህ የተነሳ የሰዎች ህይወት በማለፉ በአማራ ክልል ግጭቱን ተከትሎ ባልታወቁና ገና በመጣራት ላይ ባሉ ሃይሎች በአማራ ክልል አዊ ብሔረሰብ አስተዳደር ጃዊ ወረዳ ግጭት ተከስቶ የሰው ህይወት ሊጠፋ እንደቻለ ተናግረዋል።

በግጭቱም ከሁለቱም ብሔረሰብ የሆኑ ሰዎች ህይወት መጥፋቱን ጠቁመዋል። በድርጊቱ ተሳትፈዋል በሚል የተጠረጠሩ ግለሰቦች እየተያዙ እንደሆነም አመልክተዋል።

በተከሰተው ግጭትና ለደረሰው ጉዳት የክልሉ መንግስት የተሰማውን ሃዘን ገልጸዋል።

ችግሩን አስመልክቶ ተከታታይ የሆነ መረጃ ለህብረተሰቡ እየተሰጠ እንደሆነ ያመለከቱን አቶ አሰማኸኝ ግጭቱ ከተከሰተ በኋላ የጸጥታ ሃይሎች ወደ የአካቢዎቹ ገብተው ግጭቱን እንዲያበርዱና ወደሰላማዊ ሁኔታ መግባት እንዲቻል እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

የሁለቱ ክልሎች ርዕሰ መስተዳድሮችን ጨምሮ ከፍተኛ አመራሮች ችግሩን ለመፍታት ጥረት እያደረጉ እንደሚገኙም ጠቁመዋል።

''መከላከያ ሰራዊት ኃይል ጨምሮ በአካባቢዎቹ አሰማርቶ አካባቢውን ሰላማዊ ለማድረግ ተችሏል'' ብለዋል።

በአሁኑ ወቅትም በአካባቢው ሰላማዊ እንቅስቃሴ መኖሩን ተናግረው ችግሩን ለመፍታት የተሰራው ስራ ጥሩ ሊባል እንደሚችል ገልጸዋል።

በሁለቱ ክልሎች መካከል ያለው ግንኙነት መልካም እንደሆነ ገልጸው ከክልሎቹ የተውጣጡ ከፍተኛ ልዑክ አባላት ግጭቱ ወደተከሰተባቸው አካባቢዎች በመሄድ ማጣራት ለማድረግ፣ ለመገምገምና የመፍትሄ አቅጣጫዎችን ለማስቀመጥ እየሰሩ እንደሆነም ጠቁመዋል።

ልዑኩ በሚያቀርበው ሪፖርት መሰረት የግጭቱን አጠቃላይ ሁኔታ በማጤን በግጭቱ የተሳተፉትን በማጣራት ህጋዊ ርምጃ የሚወሰድ መሆኑን አመልክተዋል።

በአንዳንድ መገናኛ ብዙሃን በኩል እየተሰራጨ ያለው መረጃ መሰረተ ቢስ እንደሆነ የተናገሩት አቶ አሰማኸኝ ''በተለይ የአማራን ክልል ወይም ህዝብ ተጠያቂ ለማድረግ የሚሰራ ስራና የሚሰጥ መግለጫ በጣም ተገቢ አይደለም'' ብለዋል።

በወገኖች ላይ ያጋጠመው ጉዳትና የህይወት መጥፋት በክልሉ መንግስት በጽኑ የሚወገዝ መሆኑን ገልጸዋል።

የሚፈጠረውና የሚናፈሰው የሃሰት ወሬ ተገቢ አለመሆኑን አውግዘው በማህበራዊ ሚዲያ በኩል አመራሩ ስራውን በአግባቡ እንዳይሰራ የሚያደናቅፉ መልዕክቶች በዘመቻ እየተካሄዱ እንደሆነ ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም