የጋዜጠኛ ማህበሮች በሕግ ማርቀቅ ሂደቱ ላይ በቂ ተሳትፎ እንዳላደረጉ ተጠቆመ

67

አዲስ አበባ ሚያዝያ 25/20011 የኢትዮጵያ ጋዜጠኛ ማኅበሮች የመገናኛ ብዙሃን ሕጎች ላይ የሚስተዋሉ ችግሮች ማመልከቻ ሪፖርት ውይይት ሂደት ላይ ተሳትፏቸው ዝቅተኛ መሆኑን የሚዲያ ሕግ ጥናት ቡድኑ አስታወቀ።

የጋዜጠኛ ማኅበራት መሪዎች በበኩላቸው ሃሳብ እንድናቀርብ "ጥሪ ያቀረበልን አካል የለም" ይላሉ።

የመገናኛ ብዙሃን ጥናት ቡድኑ ሰብሳቢ አቶ ሰሎሞን ጎሹ ለኢዜአ እንዳስታወቁት ፤ የኢትዮጵያ ጋዜጠኛ ማኅበሮች የመገናኛ ብዙሃን ሕጎች ላይ የሚስተዋሉ ችግሮች ማመልከቻ ሪፖርት ውይይት ላይ ተሳትፏቸው ዝቅተኛ ነው።

ረቂቅ ሕጎቹ በቅርቡ ለውይይት እንደሚቀርቡም ያስታወቁት የቡድኑ ሰብሳቢ እስከአሁን በችግሮች ማመላከቻ ሪፖርት ላይ ከዘርፉ ተዋኒያን ጋር ጥልቅ ውይይት ተደርጓል። በውይይቱም የሕግ ማሻሻያዎች ግብዓት ተገኝቷል።

እንደርሳቸው ገለጻ፤ በውይይቱ ወቅት የጋዜጠኛ ማኅበራትን የሚወክሉ አመራሮች ተሳትፎ ዝቅተኛ ነው።

በተለያዩ ጊዜአት በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ጸድቀው በስራ ላይ የዋሉት የመገናኛ ብዙሃንና የመረጃ ነጻነት አዋጅ ቁጥር 590/2000፣ የብሮድካስት አገልግሎት አዋጅ ቁጥር 533/1999፣ እና የኮምፒዩተር ወንጀል አዋጅ ቁጥር 958/2008ን አዋዛጋቢ መሆናቸው ነው የችግሮች ማመላከቻ ሪፖርቱ ያተተው።

ከችግሮች ማመላከቻ ሪፖርት መሰረት ሕጎቹ በረቂቅ ደረጃም ሆነ ታውጀው በሥራ ላይ ሲውሉ በይዘታቸው፣ በአተገባበራቸው፣ አወዛጋቢነታቸው ይበልጥ ጨምሯል። 

በተለይም ሕጎቹ “መሰረታዊ የዜጎችን መብቶች ለማጣበብና ዘርፉን ለማዳከም ምክንያት ሆነዋል” በሚል ብዙ ትችት ሲቀርብባቸው መቆየቱንም ያስረዳል።

ከዚህም በመነሳት፣ መንግሥት እነዚህን ሕጎች መልሶ መፈተሽና ችግሮቹን መለየት እንደሚገባ በማመኑ ከነሐሴ 2010 ዓ.ም ጀምሮ ሕጎቹን የሚያሻሽሉ የመገናኛ ብዙሃን ሕግ ባለሙያዎች ቡድን አቋቁሞ ወደ ሥራ ገብቷል።

የመገናኛ ብዙሃን ጥናት ቡድኑ ሰብሳቢ አቶ ሰሎሞን እንደገለጹት፤ የቡድኑ አባላት በፍቃደኝነት የሚሰሩና የመገናኛ ብዙሃን ሕጎችን በተመለከተ አግባብነት ያለው ልምድ ያላቸው ጋዜጠኞች፣ በዘርፉ ምርምር ያደረጉ የሕግ ምሁራንና የዩኒቨርሲቲ መምህራን፣ የመብት ተሟጋቾችና ሌሎች ባለሙያዎች የተዋቀረ ነው፡፡

የጥናት ቡድኑ 15 አባላት ያሉት ሲሆን፤ በዘጠኝ ወር ቆይታው ዘርፉን የተመለከቱ ጥናቶችን ጨምሮ የመገናኛ ብዙሃን ሕጎች ያለባቸውን ክፍተቶች የለየ ሪፖርት በማዘጋጀት ለውይይት አቅርቧል።

እንደአቶ ሰለሞን ገለጻ፤ በጥናቱ ዋነኛዎቹ የመገናኛ ብዙሃን ሕጎች በይዘታቸውም ሆነ በአተገባበራቸው በዘርፉ ተዋንያን ላይ ከፍተኛ ጫና መፍጠራቸው ተመላክቷል። ዘርፉም እንዲዳከም አስተዋጽኦ አድርጓል።

"ችግሩን ለመፍታት የጥናት ቡድኑ አባላት ያቀረቡት ዋነኛ የመፍትሔ ሃሳብ አዋጆቹን በተሻሉ ሕጎች መተካት ነው" ብለዋል።

በጥናቱም የህጎቹ ያለፉት ዓመታት አተገባበርን በመዳሰስ፣ መሻሻልና መስተካከል የሚገባቸውን ጉዳዮች በመለየት፤ የሚሻሻሉበትንና የሚስተካከሉበትን አቅጣጫ ተቀምጧል፡፡

ቡድኑ ይህን በሚያከናውንበት ወቅት ግን የጋዜጠኞች ማህበሮች የራሳቸውን ሚና ለመጫወት አልቻሉም።

የመገናኛ ብዙሃን የሕግ ረቂቆች በመጠናቀቅ ላይ እንደሆኑ የሚናገሩት ሰብሳቢው፤ ማህበሮቹ "በረቂቁ ውይይት ላይ የጎላ ድርሻ ይኖራቸዋል" ብለው እንደሚያምኑም ተስፋ አድርገዋል።

የመገናኛ ብዙሃን ሕጎች የችግሮች ማመላከቻ ሪፖርት ላይ በቂ ተሳትፎ አላደረጉም የተባሉት የጋዜጠኛ ማኅበሮች ኃላፊዎችን በስልክ በተደረገ ውይይት የጋዜጠኛ ማህበሮችን እንደገና ለማጠናከር የተለያዩ ተግባራት እያከናወኑ በመሆናቸው በአካል ተገኝተው መልስ ለመስጠት እንደሚቸገሩ አስረድተዋል።

ይሁን እንጂ በካሜራ በተደገፈ መልኩ መልስ ለመስጠት ያልቻሉት የኢትዮጵያ ጋዜጠኞች ማኅበር ፕሬዚዳንት አቶ መሠረት አታላይም ሆኑ የኢትዮጵያ ነፃ ጋዜጠኞች ሰብሳቢ አቶ ወንድወሰን መኮንን በስልክ በሰጡን ምላሽ፤ ለውይይት እንዳልተጋበዙና ስለጉዳዩም እንደማያውቁ ነው የገለጹት።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም