የሰራተኞችን የሙያ ደህንነት በመጠበቅ በኩል ክፍተቶች አሉ ተባለ

126

ሚያዚያ 25/2011 በኢትዮጵያ የሰራተኞችን የሙያ ደህንነት በመጠበቅ በኩል ክፍተቶች መኖራቸውን የሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ገለጸ

ከአገሪቷ እድገት ጋር ተያይዞ እየመጡ ያሉ የስራ እድሎችን ከሰራተኞች የሙያ ደህንነት ጋር ማጣጣም ትኩረት ሊሰጠው ይገባልም ብሏል። 

ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ በየአመቱ ሚያዚያ 26 የሚከበረውን የሰራተኞች የሙያ ደህንነትና ጤንነት ቀን በፓናል ውይይት አክብሯል።

በውይይቱ በአለማችን የኢንዱስትሪና ሌሎች ፕሮጀክቶች እድገት በፈጣን እድገት ላይ ላለው የህዝብ ቁጥር የስራ እድል ምንጭ መሆኑ ትልቅ እድል መሆኑ ተጠቅሷል።

በአለማችን በየአመቱ ከ2 ነጥብ 7 ሚሊዮን በላይ ሰዎች ሞትና ከ374 ሚሊዮን በላይ የተለያዩ ደረጃ ጉዳት እየደረሰ መሆኑን የአለም ጤና ድርጅት ጥናት ያመለክታል።

የኢትዮጵያ ሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ተወካይ አቶ ፍቃዱ ገብሩ እንዳሉት

በኢትዮጵያ እየመጣ ካለው ሁለንተናዊ እድገት ጋር ተያይዞ በርካታ የስራ እድል እየተፈጠረ ቢሆንም የሰራተኞችን የሙያ ደህንነትና ጤንነት በመጠበቅ ረገድ ግን ክፍተት መኖሩን የሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ተወካይ አቶ ፍቃዱ ገብሩ አንስተዋል።

በተለይም በኮንስትራክሽን ዘርፍ፣ በኢንዱስትሪ፣ በዘመናዊ እርሻና መሰል ዘርፎች በርካታ የስራ እድል እየተፈጠረ ቢሆነም የሙያ ደህንነት ጥበቃ ባለመደረጉ የተጎጂዎች ቁጥርም እየጨመረ መጥቷል።

ችግሩን ለመቀነስ በሰራተኞች የሙያ ደህንነትና ጤና ላይ በቂ ግንዛቤ መፍጠር፣ ለዚህም መንግስት፣ አሰሪዎች ማህበራትና የሰራተኞች ማህበራት በቅንጂት መስራት ይጠበቅባቸዋል ብለዋል።

የኢንሹራንስ ተቋማትን ጨምሮ ሌሎች ጉዳዮ የሚመለከታቸው አካላትም ችግሩ ከተከሰተ በኋላ ምላሽ ከመስጠት ይልቅ በቅድመ መከላከል ላይ ያተኮረ ስራ መስራት ይጠበቅባቸዋል ነው ያሉት።

የሰራተኛና ማህበራዊ ሚኒስቴር ሁሉንም ተቋማት ለመቆጣጠር የአደረጃጀትና የሰው ሃይል አቅሙም የሚፈቅድ ባለመሆኑና በመንግስት ብቻ ለመተግበር አስቸጋሪ በመሆኑ የግሉ ዘርፍ ሊሳተፍ የሚችልበትን የህግ ማሻሻያ እየተደረገ መሆኑንም ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም