የሰሜን ተራሮች ብሄራዊ ፓርክን የአደጋ ስጋቶች ለመቀነስ ከእስራኤል ዮኒቨርሲቲዎች ጋር ለመሥራት ስምምነት ተደረሰ

142

ሚያዝያ  25/ 2011 የሰሜን ተራሮች ብሄራዊ ፓርክን የአደጋ ስጋቶች ለመቀነስ ከእስራኤል ዩኒቨርሲቲዎች በትብብር ለመሥራት  ስምምነት መደረሱን የፓርኩ ጽህፈት ቤት ገለጸ።

 የአሥራኤል ደን ባለሙያዎችን ያካተተው የልኡካን ቡድን አባላት ፓርኩን ጎብኝተዋል።

በጽህፈት ቤቱ የህብረተሰብና ቱሪዝም ኃላፊ አቶ ታደሰ ይግዛው ለኢዜአ እንደገለጹት  ምሁራኑ በጥናትና ምርምር የተደገፈ የመፍትሄ ሃሳብ እንዲያቀርቡ ስምምነት ላይ ተደርሷል።

በዚህም በፓርኩ ዳግም ቃጠሎ እንዳይከሰትና ከተከሰተም ጉዳት ሳያደርስ ፈጥኖ ለመከላከልና ለመቆጣጠር ያስችላል።

የእሳት አጥፊ ባለሙያዎችን ከማሰልጠን ጀምሮ የእሳት አደጋ ተከላካይ ግብረ ኃይል በማቋቋም የእውቀትና የቴክኖሎጂ ድጋፍ ይደረጋል ብለዋል።

የእስራኤል የብዝሃ ህይወት ተመራማሪዎች በቃጠሎ ሳቢያ ጉዳት የደረሰባቸውን የፓርኩን የእጸዋት ዝርያዎችን በቤተ-ሙከራ ፍተሻ በማድረግ ዳግም የሚያገግሙበትን ሁኔታ እንደሚመቻች ኃላፊው አስታውቀዋል።

ፓርኩን በተሻለ መንገድ ለማልማትና ለመጠበቅም በእስራኤል የሚገኙ ቤተ-እስራኤላውያን ያቋቋሙት የፓርኩ አጋሮች ማህበር ችግኝ እንደሚተክሉም ተናግረዋል፡፡

የደባርቅ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶክተር ጀጃው ድማሙ በበኩላቸው ዩንቨርሲቲው በፓርኩንደህንነትና ዘላቂ ልማት  የሚያተኩር የትምህርት ክፍል በማቋቋም የፓርኩን ባለሙያዎች አቅም ለመገንባት መዘጋጀቱን አስታውቀዋል።

የእስራኤል የእሳት ማጥፊያ ብርጌድ አባላት በፓርኩ ዳግም ተቀስቅሶ ከቁጥጥር ውጪ ሆኖ የነበረውን እሳት በመቆጣጠር ድጋፍማድረጋቸው ይታወሳል፡፡

በፓርኩ ዘንድሮ ለሁለት ጊዜያት በተከሰተው የእሳት ቃጠሎ በ1 ሺህ 40 ሄክታር የተፈጥሮ ደንና የጓሳ ሳር ላይ ጉዳት ደርሷል፡፡

በኢትዮጵያ ብቻ የሚገኙትን ዋልያ፣ ቀይ ቀበሮና ጭላዳ ዝንጀሮን ጨምሮ የብርቅዬ የዱር እንስሳትና አእዋፋት መገኛ ስፍራ የሆነው ፓርኩ 412 ስኩየር ኪሎ ሜትር ስፋት አለው፡፡

በኢትዮጵያ የቀድሞ እስራኤል አምባሳደር በላይነሽ ዛቫዲያ የተመራው የእስራኤል የልኡካን ቡድን ለሁለት ቀናት በፓርኩ ያደረገውን ጉብኝት አጠናቆ ትናንት በደባርቅ ከተማ ሽኝት ተደርጎለታል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም