ብሪታንያ የኢትዮጵያን ምርጫ ለማገዝ ከ580 ሚሊዮን ብር በላይ ድጋፍ ልታደርግ ነው

78

ሚያዝያ 25/2011 ብሪታንያ የኢትዮጵያን ምርጫ ለማገዝ ከ580 ሚሊዮን ብር በላይ ድጋፍ እንደምታደርግ ይፋ አደረገች።

በኢትዮጵያ ይፋዊ የስራ ጉብኝት እያደረጉ የሚገኙት የብሪታንያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጀርሚይ ሃንት ከብሄራዊ ምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ ወይዘሪት ብርቱካን ሚደቅሳ ጋር ተወያይተዋል።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ በውይይታቸው ወቅት እንደተናገሩት አገራቸው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድን ለማገዝ የገንዘብ ድጋፍ ማድርጓን ይፋ አድርገዋል።

ድጋፉ የቦርዱን ምርጫ የማስፈፀም አቅም ለማጠናከር የሚያግዝ ሲሆን በምርጫ ወቅት የክትትልና ግጭት ቅድመ ማስጠንቀቂያ ስልቱን በማጎልበት የግጭት አፈታት ውጤታማነቱን ለማሻሻል ነው።

ድጋፉ በተባበሩት መንግስታትድርጅት (ተመድ) የልማት ፕሮግራም በኩል የሚተገበር መሆኑንም ገልጸዋል።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጀርሚይ ሃንት በንግግራቸው የኢትዮጵያ ዴሞክራሲ ማሻሻያዎች የሚደነቁ መሆናቸውን ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ ወይዘሪት ብርቱካን ሚደቅሳ በበኩላቸው ''የተደረገው የገንዘብ ድጋፍ በአገሪቷ ተአማኒነት ያለው ምርጫ ለማከናወን ይረዳል'' ብለዋል።

ቦርዱ ቀጣይ የሚካሄደውን ብሄራዊ ምርጫ ዓለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀና ዴሞክራሲያዊ ለማድረግ ቁርጠኛ አቋም እንዳለው ለውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ነግረዋቸዋል።

በኢትዮጵያ የተመድ አስተባባሪ አኒአስ ቹማ በኢትዮጵያ የአስተዳደር ስነ-ምህዳሩ ተጨባጭ ለውጥ ላይ መሆኑን ገልጸዋል።

ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ በተለይ የተመድ የልማት ፕሮግራም ቀጣዩን አገራዊ ምርጫ ለመደገፍ ቁርጠኛ አቋም መያዙን ጠቁመዋል።

በርካታ ባለ ድርሻ አካላትን የሚያሳትፈው በተመድ የተዘረጋው እቅድ ድጋፉንና ለማጠከርና ለውጤታማነት በጋራ መስራትን የሚያረጋግጥ መሆኑንም ጠቁመዋል።

በኢትዮጵያ የሚካሄደው ምርጫ ተአማኒነቱን ለማረጋገጥ ገለልተኛ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ አስፈላጊ በመሆኑ በሲዲሲ ፕሮጀክት በኩል ድጋፍ እንደሚደረግ በኢትዮጵያ የተመድ የልማት ፕሮግራም ተወካይ ሚስ ሉዊስ ቻምበርሊን ተናግረዋል።

ቀጣዩ ምርጫ ስኬታማ ከሆነ በኢትዮጵያ የዴሞክራሲ ስርአት ግንባታ ትልቅ እርምጃ እንደሚሆንም አስረድተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም