የኢትዮጵያ ተወላጅ የሆኑ የውጭ ዜጎች በባንክ ዘርፍ መሳተፍ የሚያስችለው የባንክ ስራ ረቂቅ አዋጅ እንዲጸድቅ ለምክር ቤት ተመራ

135

ሚያዝያ 25/2011 የሚኒስትሮች ምክር ቤት የኢትዮጵያ ተወላጅ የሆኑ የውጭ ዜጎች በባንክ ዘርፍ መሳተፍ የሚያስችለው የባንክ ስራ ረቂቅ አዋጅ እንዲጸድቅ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መራ።

የሚኒስትሮች ምክር ቤት ትናንት ባካሄደው 15ኛ አስቸኳይ ስብሰባ በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ተወያይቶ ውሳኔ አሳልፏል።

ውሳኔ ካሳለፈባቸው ጉዳዮች መካከል የባንክ ስራ አዋጅን ለማሻሻል የቀረበውን ረቂቅ አዋጅ መርምሮ እንዲጸድቅ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መምራት አንዱ እንደሆነ ከጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት የተገኘው መረጃ ያሳያል።

የማሻሻያ ረቂቅ አዋጁ ዋነኛ ዓላማ የኢትዮጵያ ተወላጅ የሆኑ የውጭ ዜጎች በባንክ ዘርፍ ውስጥ መሳተፍ እንዲችሉ፣ ባንኮች በአገር ውስጥም ሆነ ከውጭ አገር ገንዘብ በማሰባሰብ በተለያዩ የልማት ዘርፎች እንዲውል በማድረግ በአገሪቱ የኢኮኖሚ ልማት ከፍተኛ ሚና እንዲጫወቱ ለማድረግና ባንኮች በአገሪቱ ኢኮኖሚ የክፍያና የክፍያ አፈጻጸም ስርዓት ውስጥ ቁልፍ ሚና እንዳላቸው የሚያሳይ ነው።

በዚሁ መነሻ ዓላማ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ያቀረበውን የባንክ ስራ ረቂቅ አዋጅ የሚኒስትሮች ምክር ቤት መርምሮ ረቂቁ ይጸድቅ ዘንድ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መርቷል።

ከዚህ በተጨማሪም የሚኒስትሮች ምክር ቤት ባካሄደው አስቸኳይ ስብሰባ የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ያቀረበውን የንግድ ምዝገባ ፈቃድ ረቂቅ አዋጅ አንዳንድ ማስተካከያ ተደርጎበት ይጸድቅ ዘንድ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ተመርቷል።

የጅምላ ጨራሽ መሳሪያዎችን በገንዘብ ለመደገፍ ጥቅም ላይ የዋሉ ገንዘቦችን ለማገድ በአዋጅ ቁጥር 1132/2011 አንቀጽ 9 መሰረት በሰላም ሚኒስቴር በተዘጋጀ የሚኒስትሮች ምክር ቤት ትዕዛዝ ላይ ተወያይቶ ማሻሻያዎችን በማከል ስራ ላይ እንዲውል ወስኗል።

የሰነዶች ማረጋገጥና ምዝገባ አገልግሎት ክፍያዎችን ለመወሰን በቀረበው ረቂቅ ደንብ እና የጂኦተርማል ሀብት ልማት ረቂቅ ደንብ ላይ ተወያይቶ ስራ ላይ እንዲውል ውሳኔ አሳልፏል።

ምክር ቤቱ ስለ አሰሪና ሰራተኛ ጉዳይ በተዘጋጀ ረቂቅ አዋጅ ላይ በዝርዝር ተወያይቶ ማሻሻያዎችን በማከል እንዲጸድቅ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንዲተላለፍ ወስኗል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም