በትግራይ የመልካም አስተዳደር ችግሮች በሚታዩባቸው መዋቅሮች ላይ እርምጃ እየተወሰደ ነው

54

ሚያዝያ 24/2011 በትግራይ ክልል የመልካም አስተዳደር ችግሮች በስፋት በሚታዩባቸው የአስተዳደር መዋቅሮች ላይ እርምጃ መወሰድ መጀመሩን የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳደር ዶክተር ደብረጽዮን ገብረ ሚካኤል አስታወቁ።

ምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ  ትናንት ማምሻውን በወቅታዊ ጉዳይ በሰጡት መግለጫ ላይ እንዳሉት የክልሉ መንግስት ባለፉት ወራት ሰላምን ከማስጠበቅ በተጓዳኝ  የመልካም አስተዳደር ችግሮች መነሻ የሆኑትን በመለየት የማስተካከያ እርምጃ ወስዷል።

"በክልሉ ገጠር አካባቢዎች ከመሬት አስተዳደር ጋር ተያይዞ የነበረው መዋቅር ዋንኛ ችግር ነበር" ያሉት ዶክተር ደብረጽዮን  የችግሩ ምክንያት ሆነው የቆዩ የመሬት አስተዳደር መዋቅሮች ሙሉ በሙሉ እንዲፈርሱ መደረጉን አስረድተዋል።

በክልሉ ውስጥ የገጠር አስተዳደሮች በበጎ ፈቃደኞች ይመሩ እንደነበር አስታውሰው ይህም በሂደት የህዝብ  አገልግሎትን እየጎዳው መምጣቱ በተካሄደው ጥናትና ከህዝብ ጋር በተደረጉ ውይይት መረጋገጡን  ተናግረዋል።

ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት በየቀበሌው በህዝብና ምክር ቤቶች የሚመረጡ ቋሚ ሰራተኞች እንዲቀጠሩ እየተደረገ ነው።

በቅጥሩ የተካተቱ ሰራተኞች አብዛኛዎቹ የመጀመሪያ ዲግሪ ያላቸው ወጣቶች ናቸው።

በማህበራዊ ፍርድ ቤት የነበረው የአገልግሎት አሰጣጥ ሌላው የክልሉ ህዝብ ከሚማረርባቸው መዋቅሮች መካከል አንዱ እንደሆነ አመልክተዋል።

የህግ ጉዳዮችን ወደ መደበኛ ፍርድ ቤት እንዲዛወሩ በማድረግ በማህበራዊ ፍርድ ቤቶች ይሰጡ የነበሩ አገልግሎቶች እንዲቀነሱ ተደርጓል።

ህብረተሰቡ በፍትህ አሰራሮች ላይ የሚማረርበት ሁኔታ በማጥነት በእርቅ የሚያልቁ ጉዳዮች ተሰሚነት ባላቸው የአካባቢው ሽማግሌዎች እንዲከናወኑ መደረጉን ምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ አስታውቀዋል።

 በችግሩ አፈታት ላይ ቅሬታ የሚኖረው አካል በአጭሩ እልባት የሚያገኝበት  አሰራር መዘርጋቱን ተናግረዋል።

በክልሉ ያለውን የመኖሪያ ቤት እጥረት ለማቃለልም ህብረተሰቡ ተደራጅቶ ገንዘቡን እንዲቆጥብና የመስሪያ ቦታ ለማግኘት ቅድመ ሁኔታ ከወዲሁ እንዲያሟላ እየተደረገ ነው።

ዶክተር ደብረጽዮን ከተመዝጋቢዎች መብዛት ጋር ተያይዞ መሬት ይወሰድብናል በሚል  በአርሶ አደሮች ዘንድ ስጋት  መፈጠሩን አስታውሰዋል።

አርሶ አደሮች የተሻለ ህይወት እንዲኖሩ እንጂ ተፈናቅለው ወደ ከፋ ድህነት የሚገቡበት ስርዓት እንዲኖር የመንግስት ፍላጎት አለመሆኑን  አስታውቀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም