በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል በዳንጉር ወረዳ በተከሰተው ግጭት የተጠረጠሩ ግለሰቦችን ለፍርድ ለማቅረብ እየተሰራ ነው

139

ሚያዝያ 24/2011 በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል መተከል ዞን ዳንጉር ወረዳ ተከስቶ ከነበረው ግጭት ጋር ተያይዞ በወንጀል የተጠረጠሩ ግለሰቦችን በአጭር ጊዜ ውስጥ ለፍርድ ለማቅረብ እየተሰራ መሆኑን የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን አስታወቀ።

በተከሰተው ግጭት የተጠረጠሩ ግለሰቦች ቁጥር 33 መድረሱ ታውቋል።

የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽነር መሐመድ ሃመደኒል ዛሬ ለኢዜአ እንደተናገሩት በዳንጉር ወረዳ ተከስቶ በነበረው ግጭት የተፈጸመውን ወንጀል ከክልል እና ከፌደራል ፖሊስ የተውጣጣ ቡድን ምርመራ እያደረገ ነው፡፡

የምርመራ ቡድኑ 100 የሚጠጉ የቀስት ደጋን ከነመወርወሪያው እንዲሁም 100 መጥረቢያ እና ገጀራ በቁጥጥር ሥር መዋሉን ገልጸዋል፡፡

የምርመራ ቡድኑ በአጭር ጊዜ ጉዳዩን ወደ ፍርድ ቤት በማቅረብ የግጭቱ ተጎጂዎች ፍትህ እንዲያገኙ ለማድረግ እየሰራ መሆኑን አስታውቀዋል።

ግጭቱ ከተከሰተበት ሚያዚያ 17 / 2011 ዓ.ም. ጀምሮ አካባቢው በፌደራልና በክልሉ የጸጥታ አካላት በቁጥጥር ስር በመዋሉ የአካባቢው ጸጥታ ከቀን ወደ ቀን መሻሻል ማሳየቱን ኮሚሽነሩ አመልከተዋል።

በአሁኑ ወቅት በአካባቢው ከጸጥታ ኃይሉ አቅም በላይ ሆኖ ጥቃት የሚያደርስ አካል ባለመኖሩ ህብረተሰቡ እንዲረጋጋም መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡

በማምቡክ ከተማ እና አካባቢው በሚገኙ የገጠር ቀበሌዎች የተጀመረው ህዝባዊ የውይይት መድረክ ተጠናክሮ እንደቀጠለ ኮሚሽነሩ አስረድተዋል፡፡

ከግጭቱ ጋር በተያያዘ በወንጀል የተጠረጠሩ ግለሰቦች ቁጥር 33 መድረሱን ያመለከቱት ኮሚሽነሩ ከተጠርጣሪዎች መካከል አንዱ የክልሉ ፖሊስ አባል እንደሆነ ጠቁመዋል።

በማምቡክ ከተማ አቅራቢያ አይሲካ ቀበሌ በተፈጠረው ግጭት የአስር  ሰዎች ህይወት ማለፉን ፖሊስን ዋቢ በማድረግ ኢዜአ በወቅቱ ዘግቧል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም